የሕፃናት ደህንነት፣ ትምህርትና የወደፊት ተስፋ ማዕከል የሆነቸው የአፍሪካ መዲና – አዲስ አበባ

AMN-ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ የሕፃናትን ሁለንተናዊ እድገት፣ ትምህርትና ደህንነት በከተማዋ የልማት ማዕከል በማድረግ ፈጣንና አርአያነት ያለው ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች።

የከተማ አስተዳደሩ ሕፃናትን የመንከባከብና የማህበራዊ ልማት ስራዎችን ከተማዋን የማስዋብና የማዘመን ስራ ጋር በማቀናጀት፣ ለወደፊቱ ትውልድ ጠንካራ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ አዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችውን የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) የ2026 የአመራሮች ፎረም ተሳታፊዎችን ተቀብለው ከኢኒሼቲቩ መሪዎችና ተሳታፊዎች ጋር በመሆን በልዩ ሁኔታ የተገነባውን የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከል መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤አዲስ አበባን በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኛ ነው፡፡

በሕፃናት እድገት ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በማጠናከር፣ የሕፃናትን ደህንነት፣ ትምህርትና የወደፊት ሕይወት በከተማችን የልማት አጀንዳ ማዕከል ላይ አስቀምጠናልም ብለዋል፡፡

የሕፃናት እድገት ከፅንስ ጀምሮ እስከ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የሚደረግ እንክብካቤ ለቀጣይ አስተሳሰባቸውና ጤናቸው ወሳኝ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህፃናት ማህበራዊና አእምሯዊ እድገትን ለማፋጠን ዘመናዊ የሕፃናት ማቆያና ማበልጸጊያ ማዕከላትን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመገንባት ላይ ይገኛል። ዛሬ የተመረቀው ማዕከልም የአፍሪካ ከተሞች በምሳሌነት ሊወስዱት የሚችሉትን ነው።

የከተማ አስተዳደሩ በሕፃናት ትምህርትና ደህንነት ዙሪያ የወሰዳቸው ቁልፍ እርምጃዎችም፤ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ከተማሪዎች ማቋረጥና ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ቀርፏል።

ይህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ያለ ስጋት ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አስችሏል። ምቹ፣ አረንጓዴና ለህፃናት እድገት ተስማሚ የሆኑ የትምህርት አካባቢዎችን መፍጠር ተችሏል።

አዲስ አበባን ለአህጉሪቱ አርአያ የሚያደርጋት ሌላው ስራ የከተማዋን መልክዓ-ምድር ለሕፃናት እድገት በሚመች መልኩ ማዘጋጀቱ ነው።

ይህም፣ የህፃናት መጫወቻ ፓርኮችና የስፖርት ማዕከላት መስፋፋት፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ ግንባታዎች ደህንነታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ መደረጉ፣ ለአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ምቹ የሆኑ አገልግሎቶች መዘርጋታቸው ነው፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) ፎረምን ለሁለተኛ ጊዜ ማስተናገዷ፤የከተማዋ አስተዳደር በሕፃናት ልማት ላይ ያሳየውን አህጉራዊ እውቅና ያጎናጸፈ ነው።

ከአፍሪካ ከተሞች ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ ትምህርት የመውሰጃና አርአያ የመሆን እድል ፈጥሯል።

ሕፃናትን ማእከል ያደረገች ከተማ፣ ለሁሉም ምቹ ከተማ ናት የሚለውን ሀሳብ በተግባር በማስመስከር አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች አርአያ በመሆን ላይ ትገኛለች።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review