AMN – መስከረም 27/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄዷን ተከትሎ አዲስ የመደመር መንግሥት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም ተመስርቷል።
የተሳካ መንግሥታዊ ምስረታ እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅዶች እውን ሊሆኑ የሚችሉት በመንግሥት እና በህዝብ መካከል ባለው ጤናማ ትብብርና በጋራ ቁርጠኝነት ነው።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ እንዳብራሩት፤ አዲሱ መንግሥት በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ሰላምና ጸጥታ፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር፣ ማህበራዊ ልማትና ጥበቃ፣ መሠረተ ልማት፣ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የታክስ አስተዳደር፣ የፌደራልና የክልሎች ቅንጅት፣ እንዲሁም በውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እና የሶሺዮሎጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የትኛውም መንግሥት የላቀ ዕቅድ ቢያወጣም ስኬቱ የሚወሰነው በተቋማት የቁርጠኝነት ሥራ እና በህዝቡ የተቀናጀ አጋርነት ላይ ነው።

የሀገር እድገት የሚለካውም በዜጎች ንቁ ተሳትፎ እና በህብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት ልክ ሲሆን፤ ስለዚህ ዜጎች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ተመልካች ብቻ ሳይሆኑ የለውጡ ባለቤት በመሆን በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል።
ህግን ማክበር እና ሰላምን ማስጠበቅ፡ በማህበራዊ ግንኙነቶችም ሆነ በዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ሰላምን ከሚጎዱና ከተሳሳቱ መረጃዎች ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ከዜጎች የሚጠበቁ ሐገራዊ ኃላፊነቶች ናቸው።
በተጨማሪም በትምህርት እና በሙያ መስክ በትጋት በመሳተፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የራስን ድርሻ ማበርከት ይገባል።
በሌላ በኩል በአስተዳደር ሳይንስ ንድፈ-ሀሳብ መሠረት፣ ተቋማት ለዘመኑ ፈተናዎች የሚሰጡትን ምላሽ የሚወስነው ቀልጣፋ አሰራር ነው።
በመሆኑም አስፈፃሚ መዋቅሮችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በፈጣን አሰራር በመፈጸም፣ አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በማስወገድ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
አዲሱ የመደመር መንግሥት ያስቀመጣቸውን ግቦች ከግብ ለማድረስም የእነዚህ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ ነው።
በአስማረ መኮንን