የአዲስ አበባ የሰው ተኮር ልማት እውነታ፣ ከተማሪዎች ምገባ እስከ አህጉራዊ የቀዳማይ ልጅነት አርአያነት

You are currently viewing የአዲስ አበባ የሰው ተኮር ልማት እውነታ፣ ከተማሪዎች ምገባ እስከ አህጉራዊ የቀዳማይ ልጅነት አርአያነት

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተካሄዱት የልማት እንቅስቃሴዎች ከወትሮው የከተማ ልማት ባሻገር፣ ሰው ተኮር ልማትን ማዕከል ያደረገ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እውን ተደርጓል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን የዕለት ተዕለት ህይወት የሚያቀልሉ፣ ማህበራዊ ፍትህን የሚያረጋግጡ እና በተለይም የነገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ በጥንካሬ የሚቀርፁ ዘለቄታዊ ፕሮጀክቶችን በስፋት በመተግበር ላይ ይገኛል።

የከተማ አስተዳደሩ ለአዲሱ ትውልድ ሁለንተናዊ እድገት ቅድሚያ መስጠቱን የሚያሳዩ በርካታ አበይት ተግባራት በመዲናዋ ተተግብረዋል።

ከእነዚህም መካከል በከተማዋ ስር በሚገኙ የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 1 ሚሊየን ለሚጠጉ ተማሪዎች በየቀኑ ነፃ የምግብ አገልግሎት እንዲሁም ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ፣ የደንብ ልብስ እና ቦርሳ እንዲያገኙ መደረጉ የተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ መቅረት በእጅጉ ቀንሶታል።

ዘመናዊ የህፃናት ማቆያ እና የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ማዕከላት በመገንባታቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶች ልጆቻቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲቆዩ በማድረግ ወደ ስራ ለመሰማራት እድል ፈጥሯል።

የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት፣ የየክፍለ ከተማው የህዝብ ቤተ-መጻሕፍት፣ የወጣቶች የክህሎት ማበልፀጊያ እና የስፖርት ማዕከላት ወጣቶች እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እያደረጉ ሲሆን፣ በቅርቡ የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች እና የህዝብ ፓርኮች ደግሞ ለህፃናትና ወጣቶች ጤናማ የስነ-ልቦና እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።

በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራምን መሰረት በማድረግ የተከናወኑት ተግባራት የሀገር ውስጥ ስኬት ብቻ ከመሆን አልፈው፣ ለመላው አፍሪካ አህጉር አርአያና የልምድ መቅሰሚያ መሆናቸው ተረጋግጧል።

አዲስ አበባ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የፖሊሲ አውጪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የተሳተፉባቸውን ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤዎችን በስኬት በማስተናገድ ልምዷን ለአህጉሩ አካፍላለች።

በጉባኤዎቹ ላይ የታደሙት አህጉራዊ ተወካዮች እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ህፃናትን ለማሳደግ ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ የከተማ ከባቢ በመፍጠር፣ የመጫወቻ ቦታዎችን በማስፋፋትና የወላጆች ድጋፍ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ረገድ ያሳየችው የፖሊሲ ቁርጠኝነትና የተግባር ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ ተስፋና አዲስ አቅጣጫ ያሳየ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ መድረኮች እንደተናገሩት፣ ሰው ተኮር ልማት ማለት የሰውን ህይወት የሚቀይር፣ ድህነትን የሚዋጋ እና ትውልድን የሚገነባ ልማት ነው፣ ህፃናት በረሃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሊስተጓጎሉ አይገባም” ማለታቸው ዘይዘነጋም፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የተማሪዎች ምገባ ኤጀንሲን በማቋቋም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህፃናት በየቀኑ በቂ ምግብ አግኝተው እንዲማሩ ያደረገ ሲሆን፣ ለበርካታ እናቶችም የስራ እድል ፈጥሯል።

በተመሳሳይም ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚገነባው ዛሬ በህፃናት ላይ በሚደረግ የትምህርት፣ የጤና እና የስነ-ልቦና ኢንቨስትመንት ነው የሚለው የከንቲባዋ አቋም፣ በትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያ፣ በኮምፒውተርና ላቦራቶሪ ቁሳቁሶች ማሟላት እንዲሁም በንፅህና መጠበቂያ ግንባታዎች አማካኝነት በተጨባጭ ተግባር ላይ ውሏል፡፡

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው ሰው ተኮር ልማት በሰው ላይ የሚደረግ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት በመሆኑ፣ አስተዳደሩ የተናገረውን በተግባር በመተርጎም ከተማዋን ለህፃናትና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ለአዲሱ ትውልድ፣ ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ህዳሴ እንዲሁም ለመላው አፍሪካ ሁለንተናዊ እድገት አስተማማኝ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review