AMN – ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የቆዩ ውስብስብ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ውዝግቦችን በዘላቂነት ለመፍታት ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በተመረጡ 8 አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ከአንድ ወር በላይ ሲካሄድ የቆየው ይህ የምክክር ጉባዔ፣ አጀንዳዎችን የማጣጣምና ግብዓት የመሰብሰብ ሥራውን አጠናቋል። 4 ሺሕ ጉባኤተኞች በተገኙበት የሂደቱ የመጨረሻ ሰነድ ዛሬ ይፋ ይደረጋል።
ይህ የምክክር ሂደት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ሁሉን አቀፍ ዕድገት ቁልፍ መፍትሄ እንደሚያመጣ ከፍተኛ እምነት ተጥሎበታል። ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሲካሄድ የከረመው ይህ መድረክ፣ ለሀገሪቱ መሰረታዊ ጥያቄዎች የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦችን ሲያፈልቅ ቆይቷል።
ይህ ሂደት በዋናነት በታሪክ ትረካዎች፣ በስርዓተ-መንግሥት ግንባታ እንዲሁም በሌሎች ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የቆዩ ልዩነቶችን ለመፍታት እና የጋራ ትርክትና ራዕይን ለመገንባት ያለመ ነው።

በምክክሩ በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን በማጠናከር፣ ለወደፊት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ ጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፎችን የመዘርጋት ዓላማም ተሰንቋል።
የምክክሩ ውጤቶች እንደ የጋራ ድል ሊወሰዱ እንደሚገባ ኮሚሽኑ መግለጹ የሚታወስ ነው። ስምምነት የተደረሰባቸው አጀንዳዎች ቀጣይነት ባለው ህጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃዎች የሚፈጸሙ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል።
የዚህ ታላቅ ሂደት ስኬት መንግስት የምክክር ውጤቶችን ወደ ህግ እና ፖሊሲ የመቀየር ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።
በተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ግላዊና ጊዜያዊ ጥቅምን ወደ ጎን በመተው፣ አውዳሚ የሆኑ የግጭት ትርክቶችን ወደ አብሮነት ትረካ እንዲቀይሩ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደት የሁሉም ዜጋ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ የሂደቱ ስኬታማነት የሚለካው የጋራ መግባባትን እና የሀገርን ህልውና በሚያረጋግጥ መልኩ ሊሆን ይገባል።
በበረከት ጌታቸው