አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እና የአዲስ አበባ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እና የአዲስ አበባ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ እና ሙስናን በመከላከል ረገድ በግንባር ቀደምትነት ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።

ኮሚሽኑ፣ የፀረ-ሙስና ትግሉን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ብልሹ አሠራሮችን ከመሠረቱ ለማስወገድ፣ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክን ጨምሮ ከ13 ባለድርሻ ተቋማት ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ፣ በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስናን በዘላቂነት በመከላከል ረገድ ስኬታማና ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ እና አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በሙስና የተገኘ ሀብት ማስመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞ በመከላከል ሥራዎች ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉን ጠቁመው፣ ይኸው ጥረት በበለጠ አቅም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል።

ሙስና የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሳይመርጥ ሁሉንም የሚያጠቃ በመሆኑ፣ በመከላከል ሂደቱ የሁሉም ዜጎችና ተቋማት ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ይህን ተቋማዊ ትስስር ወደ ተግባር ለመቀየር ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፤ ሕብረተሰቡ በሥነ-ምግባር የታነጸ እንዲሆን ግንዛቤ ማዳበር፣ ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥና ቀድሞ በመከላከል ረገድ ሚዲያው ያለውን ሰፊ ተደራሽነትና የማንቃት አቅም በቅንጅት እንደሚጠቀምበት ተገልጿል።

በዚሁ መሠረት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሙስና አስከፊነት እና በበጎ እሴቶች ዙሪያ ያተኮሩ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ፕሮግራሞችን፣ አጫጭር መልእክቶችንና ዘገባዎችን ለአየር ያበቃል ፤ ህገ-ወጥ አሰራሮችን የሚያጋልጡና የበጎ አሰራር ልምዶችን የሚያጎሉ ዘገባዎችን በማቅረብ የተቋማት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ያስችላል ፤ ለኮሚሽኑ የተለያዩ ሁነቶች በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በዲጂታል ቻናሎች በቂ የዘገባ ሽፋን ይሰጣል እንዲሁም ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ ተቋማት ላይ ጥናት በማካሄድ የምርመራ ዘገባዎችን ያዘጋጃል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review