AMN – ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች ላለፉት 100 ዓመታት ላሳዩት ታላቅ ትጋትና አገልግሎት ምስጋና ያቀረቡት ፕሬዚዳንቱ፣ ተቋሙ የሕዝብን ጤና ለማስጠበቅ የመንግስትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገርን ኢኮኖሚ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሕዝብ ጤና ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን በሚገባ እንደሚረዳ በመጠቆም፣ ለዚህም እንደ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሉ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በምሥረታ በዓሉ መድረክ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ ዛሬ የምናከብረው የአንድ ተቋም 100ኛ ዓመት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የሕብረተሰብ ጤና ሥርዓት ዕድገትና ጉዞ ጭምር ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመተባበር በወረርሽኝ ልየታ፣ በክትትል እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ረገድ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ያወሱት ዶክተር መቅደስ፣ መንግስት የሕዝብን ጤና መጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱ መሆኑን በመገንዘብ የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ኢንስቲትዩቱ የተሰጡትን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልእኮዎች በትክክል እንዲያሳካ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ መድረኩ በተቋሙ ውስጥ ባለፉት ዘመናት ያገለገሉ የቀድሞ አመራሮችን፣ ታዋቂ ተመራማሪዎችን እና ታታሪ ሠራተኞችን ለማመስገን የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዕለቱ ለሕብረተሰቡ የገባነውን ታላቅ ቃል የምናድስበት ልዩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር የተሰጠውን የበሽታዎች ክትትልና ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የድንገተኛ ሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠሪያ ማዕከላትን በየክልሎቹ በማቋቋም የወረርሽኝ መከላከል ሥራውን በግንባር ቀደምትነት እየመራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 40 የሪፈራል ላቦራቶሪዎችን ያቋቋመ ሲሆን፣ በቀጣይም የአፍሪካ የሕብረተሰብ ጤና የልህቀት ማዕከል ለመሆን በከፍተኛ ትጋት እየሠራ እንደሚገኝ መግለፃቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።