AMN – ጥቅምት 11/ 2019 ዓ.ም
ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ራሱን የትግራይ ሕዝብ ብቸኛ ተወካይና ጠባቂ አድርጎ ለማቅረብ ቢሞክርም ፣ በተግባር ግን ሕዝቡን ለቡድናዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ማስፈጸሚያነት ሲጠቀምበት ቆይቷል።
ቡድኑ ትግራይን እንደ አንድ የግል ኩባንያው በማየት የሕዝቡን የሀሳብ ነፃነት ሲቀማ ፣ የኢኮኖሚ ዕድሎችን ለጥቂት ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ሲያድል ፣ እንዲሁም የተለየ ሀሳብ ያላቸውን ወገኖች ሲያሳድድና ሲያስር ቆይቷል።
ቡድኑ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ተፈጥሯዊ የሕዝብ አንድነትን የመሸርሸር አደገኛ ስልትም ሲከተል ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከቀናት በፊት በትግሪኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፣ ህወሓት ሕዝቡን በአንድነት እንዳይቆም በየአካባቢው ራያ፣ አጋሜ ፣ እንደታ እያለ ክፍፍልን ሲፈጥርና መለያየት ሲያጎለብት ቆይቷል።
ይህ አካሄድ ድርጅቱ ለትግራይ ሕዝብ ደህንነትና እድገት ሳይሆን፣ ለራሱ ጠባብ ቡድናዊ ጥቅም ብቻ የሚቆም መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ዛሬ ላይ ህወሓት ከባድ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ሞራላዊ ውድቀት ውስጥ ይገኛል። ላለፉት ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ስም የነበረው የሐሰት ትርክት ፈራርሷል። የትግራይ ሕዝብ በስሙ የሚነግደውና ወደ አልተፈለገ ጦርነትና መከራ የሚከተው ይህ ጨቋኝ ቡድን ከጫንቃው እንዲላቀቅ እየሰራ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከቀናት በፊት በትግሪኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ያነሷቸው ነጥቦች፣ የትግራይ ሕዝብ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ሲሰቃይበት የነበረው አገዛዝ ማብቂያው እንደደረሰና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ጭላንጭል በትግራይም ለመፈንጠቅ መቃረቡን የሚያበስሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው እንዳመለከቱት ፣ ህወሓት ትግራይን እንደ ግል ኩባንያው ተቆጣጥሮ የመግዛት አካሄድ ከእንግዲህ ሊደገም አይገባም።
የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን የፖለቲካ አማራጭ በነፃነት የሚያንጸባርቅበትና የሚመርጥበት መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል።
ከህወሓት ውድቀት በኋላ ትግራይ ዳግም የአንድ ድርጅት ርስት አትሆንም። የትግራይ ሕዝብም ከተጫነበት የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ተላቆ የሚፈልገውን የፖለቲካ ፓርቲና አመራር በነፃነት የመምረጥ መብቱ ይረጋገጣል። ከእስራትና ከእንግልት ተላቆ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ይከበሩለታል። በቡድኑ የተፈጠሩት የአካባቢ ከፋፋይ ትርክቶች ፈራርሰው የትግራይ ሕዝብ አንድነትና ወንድማማችነት ይጠናከራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳረጋገጡት ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተጀመረውና እየተገነባ ያለው ዲሞክራሲያዊ ነፃነት በትግራይም መረጋገጥ አለበት። የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ጨቋኝ ቡድን መዳፍ ነፃ ወጥቶ፣ የልማቱና የሰላሙ ተጋሪ እንዲሆን በትኩረት ይሠራል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ ለሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በእኩልነት እንደሚሠራ ሁሉ ፣ የትግራይም ክልል ፈጣን የልማትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ባለቤት እንዲሆን ይሰራል፡፡
ዛሬ የህወሓት የአምባገነንነትና የጨቆና ዘመን አብቅቶለታል። ትግራይን እንደ ግል ንብረት አድርጎ የመግዛትና ሕዝቡን ለመከራ የመዳረግ አሠራር ከእንግዲህ አይደገምም።
የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ጨቋኝ ቡድን ነፃ ወጥቶ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን በሰላም፣ በዲሞክራሲና በልማት እየተገነባች ባለችው ኢትዮጵያ የራሱን ተሳታፎ ያደርጋል ፣ የልማቱም ተጋሪ ይሆናል።
በታደሰ ሽፈራው