AMN – ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም
መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ ያለው እይታ በመቀየሩ ስፖርት ወዳዱን ማህበረሰብ ከዓለም የስፖርት ውድድሮች ጋር ለማያያዝ በሰራነው ሥራ በሁለት ሳምንታት ብቻ 3 ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት ችለናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጸጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው “የሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ ውድድር በኢትዮጵያ – በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት ተካሂዷል ብለዋል።
አዲስ አበባ በታሪኳ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤መነሻውንና መድረሻውን የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ በሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ ያደረገ “የሲቲ ማውንቴን ባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ” ውድድር ከ24 በላይ ሃገራት በመጡ ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪዎች መካከል በከፍተኛ ፉክክር እና ወኔ የተካሄደ እጅግ ደማቅ ውድድር መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስፖርት ከዓለም ጋር የምንገናኝበት፣ የምንግባባበት እና ትብብርን የምናጠናክርበት አንዱና ትልቁ ዘርፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለስፖርት ዘርፍ ያለው እይታ በመቀየሩ ስፖርት ወዳዱን ማህበረሰብ ከዓለም የስፖርት ውድድሮች ጋር ለማያያዝ በሰራነው ሥራ በሁለት ሳምንታት ብቻ 3 ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማዘጋጀት ችለናልም ነው ያሉት፡፡
ውድድሩ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መዲና እና በጥቁር ህዝቦች የድል ታሪክ መታሰቢያ እንዲካሄድ ለመረጣችሁ እና ቀጣይ ዓመትም እዚሁ እንደሚካሄድ ላረጋገጣችሁልን የዓለም አቀፉ የብስክሌት ህብረት (UCI) ለዝግጅቱ ስኬት ሌት ተቀን ለደከማችሁ የስፖርት አመራሮችና አካላት በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በከፍተኛ እንግዳ ተቀባይነት ጨዋነት እና ስፓርት አድናቂነት ድጋፋቸውን ለገለጹ የከተማዋ ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡