ጎንደር ውሃ ገድባ ማየት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ጎንደር ውሃ ገድባ ማየት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጎንደር ከተማ የተገነባውን የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ምርቃት አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ ታሪካዊቷና ድንቅ ከተማ የሆነችው ጎንደር ውሃ አግኝታ ማየት በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የመገጭ ግድብ ለ19 ዓመታት ተጓትቶ የነበረና የህዝብን ውሃ ጥም በቀላሉ መፍታት ሳይችል የቆየ ፕሮጀክት መሆኑን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት ባለቤት አጥቶ በመቆየቱና ከፍተኛ ሀብት በማባከኑ «እርግማን» የሚባልለት እንደነበር ገልጸው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ኮንትራክተር በመቀየርና የተሰሩ ክፍተቶችን በማስተካከል በባለቤትነት ተጠናቆ ለምርቃት መብቃቱን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሀገሪቱ በየቦታው የሚታዩ የፕሮጀክቶች መጓተቶችና የጅምር ስራዎች አለማለቅ ዋነኛ ምክንያት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተቋማዊ አቅም የመቀየር ልምምድ ድክመት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ይህንን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍም ሉዓላዊ አቅምን መገንባት፣ ጀምሮ የማጠናቀቅ ባህልን ማዳበር እንዲሁም የፌደራልና የክልል መንግስታት በቅንጅትና በመናበብ መስራት እንደሚገባቸው በአጽንኦት ተናግረዋል።

አያይዘውም የጎንደር ህዝብ ለዘመናት የቆየውን የድህነትና የልማት እጥረት ሰንሰለት ሰብሮ ለመውጣት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በባለቤትነት መንከባከብና መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።

የጎንደር ከተማን ገጽታ ለመቀየርና የቱሪዝም መስህብነቱን ይበልጥ ለማሳደግ የማረፊያ ስፍራዎችን ጨምሮ ተጨማሪ ማሻሻያ ስራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም የመንግስት ስራ ሀገርን የመገንባት ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ስልጣኔ እውን ለማድረግ መንግስትና ህዝብ በአንድነትና በትብብር መቆም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review