AMN- ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ወንዞች የትዝታ፣ የውበት እና የህይወት መገለጫ የነበሩበትን ጊዜ የሚያስታውሱ ድንቅ የጥበብ ስራዎች ዛሬም ጆሮ ገብ ናቸው።
ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስ “ወንዜ ቀበና…” እያለ በናፍቆት የተሞላውን የስንኝ ቋጠሮ ሲቀኝ፣ የብዙዎችን የልጅነት ማስታወሻና በወንዙ መጋጠሚያዎች ላይ የነበረውን ያንን የጠራ ተፈጥሮ ነበር የገለጠው።
በተመሳሳይ የክብር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራም “ቢሻን አዲስ አበባ…” እያለ የከተማዋን ወንዞች ውበት አድንቋል።
ሆኖም ግን፣ ያ የውበት ተምሳሌት የነበረው ቀበና ለዘመናት ተፈጥሯዊ ማንነቱን አጥቶ፣ የፍሳሽ መውረጃና የቆሻሻ መጣያ ሆኖ፣ ጠረኑ አላስጠጋ ብሎ በተረሳበት የቁጭት ዘመን ውስጥ ቆይቷል።

ዛሬ ላይ ያ የቁጭት ታሪክ ተቀይሯል፤ ቀበና በትጋትና በላብ ታክሞ አዲስ ህይወት በመዝራት የከተማዋ አዲስ የውበት ማማ መሆን ችሏል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የወንዙን ወቅታዊ ገፅታና የተከናወነውን ተአምራዊ ለውጥ አስመልክተው ይህንን ብለዋል፣ “ፈጣሪ የሰጠንን ቀበና ‘ሰው’ አጠፋው፤ ይህ የተፈጥሮ ስጦታ መጥፋት ቁጭት ያደረበት ‘ሰው’ ደግሞ ቀበናን ዳግም እንደ አዲስ እንዲወለድ አደረገው።”
ከንቲባዋ አክለውም የቀበና ወንዝ ለዘመናት በዘፈን እና በትዝታ ብቻ ስሙ ሲነሳና ሲወደስ ኖሮ ዛሬ ግን ዳግም እንዲወለድ በማድረግ ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።
ትናንት የብክለት፣ የበሽታ ምንጭና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የነበሩት ወንዞቻችን ዛሬ ላይ በትጋት እና በላብ እየታከሙ፣ ለነዋሪው ተስፋንና ሀሴትን የሚለግሱ የደስታ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ታዲያ ወደ ድምጻዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ዘፈን ስንመለስ “…ወንዜ ቀበና… የማልዘነጋው ቡረቃዬ ኩሬ፣ የዋኘሁብሽ ጥንስስ ባህሬ…” እያለ የሰደረው የልጅነት የደስታ ስሜት፣ ዛሬ በቀበና ወንዝ ዳርቻ በተገነባው ማራኪ የልማትና የመዝናኛ ፕሮጀክት ላይ በተግባር እውን ሆኖ ይታያል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው ይህ ድንቅ ፕሮጀክት፣ ከሌሎች የከተማዋ ታላላቅ የኮሪደር ልማቶች ጋር ተዳምሮ አዲስ አበባን የውበት ማማ አድርጓታል።
ይህ የወንዞች ልማት ሥራ ትናንት በኪነ-ጥበብ ሥራዎች ውስጥ የነበረውን የተፈጥሮ ናፍቆት ዛሬ ላይ ህያውና የሚጨበጥ እውነታ ከማድረጉም በላይ፣ መላው የከተማዋ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች የሚዝናኑበት፣ ንፁህ አየር የሚተነፍሱበት እና የከተማዋን መታደስ በአካል የሚያዩበት ደማቅ የልማት አሻራ ሆኗል።
በያለው ጌታነህ