በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች 27 የትራፊክ መብራት መጋጠሚያዎች ላይ በጸሀይ የሚሰራ የሀይል አቅርቦት ተከላ ተከናወነ

You are currently viewing በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች 27 የትራፊክ መብራት መጋጠሚያዎች ላይ በጸሀይ የሚሰራ የሀይል አቅርቦት ተከላ ተከናወነ

AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች 27 የትራፊክ መብራት መጋጠሚያዎች ላይ በጸሀይ የሚሰራ የሀይል አቅርቦት ተከላ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የከተማዋን የትራፊክ መብራቶች ባልተቆራረጠ መልኩ አገልግሎት አንዲሰጡ ለማድረግ 27 የትራፊክ መብራት ባሉባቸው ቦታዎች ለይ የሶላር ሃይል መቀበያ መሳሪያ መትከሉን አመልክቷል፡፡

በባለስልጣን መ/ቤቱ የመንገድ ደህንነት ምህንድስና ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘይኑ ኤልያስ ቀደም ሲል በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ የትራፊክ መብራቶች ያለመስራት ችግር እንደሚገጥም ተናግረዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ ባለፉት ስድስት ወራት የትራፊክ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ በጸሀይ ሃይል የሚሰራ የሃይል አቅርቦት አንዲኖር ተደርጓል ብለዋል፡፡

የጸሃይ ሃይል /ሶላር/ የተተከለባቸው ቦታዎችም ጀርመን አደባባይ፣ ጀሞ ሚካኤል፣1 አየር ጤና፣ 18 ማዞሪያ፣ 3 ቁጥር ማዞሪያ፣ ጦርሃይሎች. ለገሀር፣ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ ብሄራዊ ትያትር፣ ኢቲቪ/ፖስታ ቤት/፣ ጥቁር አንበሳ፣ ሰንጋተራ፣ ባንኮዲሮማ፣ ፓርላማ፣ አትላስ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ አፍሪካ ህብረት፣ ትምባሆ፣ ሾላ ገበያ፣ ሾላ ፔፕሲ፤ ሳህሊተማርያም. ቦሌ ሚሊኒየም፣ ቦሌ ሱፐር ማርኬት መሆናቸውን አቶ ዘይኑ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የሶላር ሃይል አቅርቦት በጥናት እየተለየ መሳሪያው የሚተከል መሆኑን የገለጹት አቶ ዘይኑ አዲሶቹ የትራፊክ መብራት ተከላዎችን ጨመሮ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 90 ቦታዎች የትራፊክ መብራት እንዳለና የትራፊክ ፍሰቱም ሰላማዊ እየሆነ መምጣቱን መናገራቸውን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review