AMN- ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም
በጤናው ዘርፍ በ5 ዓመታት ውስጥ ባለፉት 100 ዓመታት ከተመዘገበው በእጥፍ የሚበልጥ እድገት ማስመዝገብ ተችሏል።
አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ጉዞ ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግቧል።
ከተማችን በሁለንተናዊ መልኩ እንድትለወጥ ከተሰሩ ስራዎች አንዱ በጤናው ዘርፍ የታየው የጤና መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራ ዋነኛው ነው፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ የጤና መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ የተገነቡት ዘመናዊ የአይን ሕክምና፣ የኩላሊት እጥበት እንዲሁም የፎረንሲክ እና ስነምረዛ ምርምር አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡
በዘውዲቱ ሆስፒታል እጅግ ዘመናዊ ተደርጎ የተገነባው የህክምና ልህቀት ማዕከል እና በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ውስጥ ለታካሚዎች ዘመኑን የዋጀ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ “አዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል” ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በማዕከላቱ በነባሮቹ ሆስፒታሎች በኋላቀር የህክምና መሳሪዎች እና ለታካሚዎች በማይመችና በተጨናነቀ ሁኔታ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በመቀየር የዘመኑ ቴክኖሎጂ ተሟልተውላቸው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በተጨማሪም የአበበች ጎበና እናቶችና ህጻናት ሆስፒታል፣ ላፍቶ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ ኮልፌ እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የገላን ድንገተኛ ህክምና ሆስፒታል በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ የተገነቡ የህክምና ማዕከላቶች ናቸው።

ለ4ዐ ጤና ጣቢያዎች መሰረታዊ ማስፋፊያ እና 9 አዳዲስ የጤና ጣቢያዎች ተገንብተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡
አዲሰ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ እና በጤናው ዘርፍ ያለው ፍላጎት በመንግስት ብቻ የማይሟላ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ በመደገፍም እጅግ ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች እንዲገነቡ ተደጓል።
በአጠቃላይ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ስራዎች ከ 5 ዓመት በፊት የነበሩትን አልጋዎች ቁጥር ከ 2 እጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏ፡፡
በዚህም በ 5 ዓመታት ውስጥ የታየው እድገት ባለፉት 100 ዓመታት ከተመዘገበው እድገት በእጥፍ እንዲበልጥ አድርጎታል፡፡
ጤናን የምንጠብቀው በሕክምና ብቻ ሳይሆን በመከላከል ጭምር በመሆኑ፣ አዲስ አበባን ከብክለት በመከላከል፣ ፅዱ አረንጓዴ እና ለኑሮ ተስማሚ ከተማ በማድረግ ጤናማ አካባቢን የመፍጠር የጤና ፖሊሲዋ በከተማዋ በተሟላ ሁኔታ እየተተገበረ እንደሚገኝ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡