ጤናማ ማህበረሰብ የሀገራችንን የብልፅግና ርዕይ እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና አለው-ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN-ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

በአካል የጠነከረ፤ በአእምሮ የበለፀገ እና ጤናማ ማህበረሰብ የሀገራችንን የብልፅግና ርዕይን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚና አለው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ገልፀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዛሬ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የዕድሳት፣ የማስፋፊያ እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን ስራ ፕሮጀክትን መርቀናል ብለዋል።

ባለፉት አመታት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ሰፋፊ ስራዎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

የእናቶችና ህጻናት ሞት እንዲሁም የበሽታ ስርጭት በእጅጉ መቀነሱንም አስፍረዋል።

አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው ፣ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር እየተሰሩ ከሚገኙ ስራዎች መካከል ዛሬ የመረቅነው የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዕድሳት፣ ማስፋፊያና ዲጂታላይዜሽን ስራ አንዱ ነው ብለዋል።

ማስፋፊያው ለአገልጋይና ለተገልጋዩ ምቹ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑ ግልጽ አሰራርን የሚያሰፍን፣ ለምላሽ አሰጣጥ እና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለማስፈን የሚያስችል፣ ለአዕምሮ ደስታ የሚሰጥ እና አዲስ ሀሳብ የማፍለቅ እድል የሚሰጥ የለውጥ ሀሳብ ውጤት ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው የቢሮ እድሳት፣ ማስፋፊያ እና ዲጅታላይዚሽን ስራ የላቀ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን የጤና ፍላጎት ለማሳለጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review