AMN- ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም
ፊፋ በቅርቡ ይፋ ያደረገው እቅድ ትልቅ መነጋጋሪያ ሆኗል። ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ያለው እግርኳስን በበላይነት የሚመራው ተቋም አባል ሀገራቱን ካዝናቸውን የሚሞላ እቅድ ማምጣቱን ገልጿል።
ተቋሙ የዓለም ዋንጫ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫ ውድድርን መጠነኛ ድርሻ ለባለሀብቶች መሸጥ የሚያስችል ሀሳብ አስተዋውቋል።
ፊፋ በእቅዱ መሰረት FIFA Forward Enterprises (FFE) የተሰኘ የታሰበውን ድርሻ ገቢ እና ወጪ የሚቆጣጠር አካል ይመሰርታል። ምንም እንኳን ይህ አካል ይመስረት እንጂ ሁሉ ነገር በበላይነት የሚቂጣጠረው ፊፋ ነው።
በጂያኒ ኢንፋንቲኖ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው ፊፋ ለግል ባለሃብቶች መሸጥ ያሰበው 21 በመቶ ድርሻውን ነው። ሽያጩም 4.2 ቢሊየን ዶላር ያስገኛል ብሏል።
አብዛኛው ገንዘብ እንደፊፋ እቅድ ከሆነ አባል ሀገራቱ የእግርኳስ ልማታቸውን የበለጠ እንዲያሳድጉ ይከፋፈላል። ገንዘቡም FIFA Fast-Forward Programme (FFFP) በተሰኘ አዲስ የልማት ፕሮግራም አማካኝነት ለሀገራቱ ይደርሳል። ፕሮግራሙ ገንዘቡ ለታለመለት አላማ መዋሉን የሚያረጋግጥ እና የልማት ስራዎችን የሚከታተል ነው።
የፊፋን የዓለም ዋንጫን ድርሻ የመሸጥ እቅድ ዓለም አቀፉ ባንክ ጄ ፒ ሞርጋን ያማክረዋል። ትራቫይ ካፒታል (Thrive Capital) የተሰኘው ካምፓኒ ደግሞ ባለሃብቶችን በማምጣት እና እራሱም መዋለንዋዩን ፈሰስ በማድረግ ይሳተፋል።
ትራይቭ ካፒታል የተሰኘው በሶፍትዌር እና ኢንተርኔት ላይ የሚሰራው ካምፓኒ የሚመራው የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ባለቤት የሆነው ጃረድ ኩሸነር ወንድም የሆነው ጆሹአ ኩሽነር ነው። ይሄ መረጃ ሲሰማ በርካቶች ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል።
ፊፋ ባወጣው መግለጫ እንደታሰበው ባለሃብቶች መጠነኛ ድርሻውን ከገዙ ለእግርኳስ ልማት የሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ 10 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል። 211ዱ አባል ሀገራትም ከዚህ ቀደም አይተውት ያማያውቁት ገንዘብ ወደ ካዝናቸው ይገባል። ለአንድ አባል ሀገር ከ8 ሚሊየን ዶላር ተነስቶ በየዓመቱ እያደገ እስከ 20 ሚሊየን ዶላር ያገኛል።
ይህ እቅድ ለተግባራዊነቱ በአባል ሀገራቱ እና 37 ግለሰቦች ያሉበት የፊፋ ካውንስል መፅደቅ ይኖርበታል። ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ዕድሉ ሊያመልጠን አይገባም እያሉ እየወተወቱ ይገኛሉ። እንደ ቢቢሲ ስፖርት ዘገባ አባል ሀገራቱም ምላሻቸውን እስከ መስከረም 9 እንዲያሳውቁ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል። ሀገራቱ ለእቅዱ ይሁንታቸውን ከሰጡ ለእያንዳንዳቸው 40 ሚሊየን ዶላር ይደርሳቸዋል ተብሏል።
ገና የእቅዱ ሀሳብ በዝርዝር ሳይቀርብ ተቃውሞውን ያሰማው የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ገልጿል። እቅዱን “መስመር ያለፈ” ያለው ማህበሩ አባላቱን ለአስቸኳይ ስብሰባ ይጠራል። ፊፋ ሀሳቡን ካልቀየረ አንድም የአውሮፓ ሀገር በዓለም ዋንጫ እንዳይሳተፍ ሊያደርግ እንደሚችል ዝቷል።
ሀገራትም በግላቸው በእቅዱ ዙሪያ ያላቸውን አቋም እያሳወቁ ይገኛል። እንግሊዝ እንደ አንድ የፊፋ አባል ሀገር ስለ እቅዱ ላቅ ይገባ ነበር ብላለች። ፈረንሳይም ተመሳሳይ አቋም የያዘች ሀገር ናት።
በግለሰብ ደረጃም ነቀፌታው በርክቷል። የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሃም “እግርኳስ ሸቀጥ አይደለም” ሲሉ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ መልዕክት አጋርተዋል። የቀድሞ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ሴፕ ብላተር “ማንም የእኛን ተወዳጅ ጨዋታ መሸጥ አይችልም” ብለው ተችተዋል።
ከዚህም በላይ መነጋገሪያነቱ የሚቀጥለው የፊፋ ድርሻውን ለባለሀብት የመሸጥ እቅድ እውን ሆኖ እንመለከተው ይሆን?
በሸዋንግዛው ግርማ