AMN – የካቲት- 6/2017 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀን “ሬዲዮ እና የአየር ንብረት ለውጥ” በሚል መሪ ሀሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ሬዲዮ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ነው አየር ላይ ለሥርጭት የበቃው፡፡
ዛሬም ድረስ የቴሌቪዥን እና የዲጂታል ሚዲያው ዓለምን እየተቆጣጠረ በመጣበት በዚህ ወቅት እንኳን ሬዲዮ ለበርካታ ሚሊዮን የዓለማችን ህዝቦች ተመራጭ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡
በተለይም የማህበራዊ ሚዲያው መንሰራፋት ያስከተለውን ጫና ተቋቁሞ ለዚህ መድረሱ ሬዲዮ ፈተናዎችን የሚቋቋም ጠንካራ የሚዲያ ኢንዱስትሪ መሆኑ ይነገርለታል፡፡
የዘንድሮው የዓለም ሬዲዮ ቀን ሲከበር መሪ ቃሉ “ሬዲዮና የአየር ንብረት ለውጥ” የሚል ሆኗል፡፡
ይህም ሬዲዮ ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንፃር መረጃን በማሰራጨት እና የአየር ንብረት ለውጥ እሳቤን ለማስረፅ ያለውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ዩኔስኮ በፈረንጆቹ 2011 ላይ የሬዲዮ ቀን እንዲከበር ከወሰነበት ጊዜ ጀምሮ አባል ሀገራቱ ስለሬዲዮ አበርክቶ እና በቀጣይም ስለሚኖረው አስተዋጽኦ በመምከር እለቱን ያከብራሉ፡፡
በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ስር የሚገኘውራዲዮ ጣቢያም ነሀሴ 30 /1997 ዓ.ም ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ ተብሎ በይፋ መደበኛ ስርጭቱን ጀመረ፡፡
ኤፍ ኤም 96.3 ሬዲዮም ላለፉት 20 ዓመታት የመዲናዋን ነዋሪዎች እና በዙሪያ ያሉ ማህበረሰቦችን ወቅታዊ የሆኑ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን በማድረስ በስፋት ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህን አገልግሎቱን በማጠናከርም ለውድ አድማጮቹ ወቅታዊ እና ትኩስ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራውን እንደሚቀጥል በደስታ ያበስራል፡፡
የሬዲዮ ቀን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በየዓመቱ የካቲት 6 የሚከበር ሲሆን፣ ዘንድሮም ለ14ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በማሬ ቃጦ