AMN – መጋቢት 2/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር በዛሬው እለት ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ የበከሉ ተቋማትን 2.6 ሚሊየን ብር መቅጣቱን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ፍሳሽና በካይ ቆሻሻ ወደ ወንዝ የለቀቁ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በደንብ ቁጥር 180/2017 መሰረት የገንዘብ ቅጣቶች በመቅጣት አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ እስፒሻላይዝድ ልዩ የካንሰር ህክምና ተቋም 400 ሺህ ብር፣ በወረዳ 7 ኤክስትሪም ሆቴል 300 ሺህ ብር እና ሙሉ ወንጌል አማኞች አጥቢያ ቤተክርስቲያን 100 ሺህ ብር ቅጣት መቀጣታቸውን ገልጿል።

በተጨማሪም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሙኒዝ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት 300 ሺህ ብር፣ አል ሐኪም ቢዝነስ ድርጅት 400 ሺህ ብር እና ታዬ ቦጋለ የግል ድርጅት 100 ሺህ ብር ሲቀጡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ፍቅር ፕላዛ 100 ሺህ ብር ተቀጥተዋል።
በተያያዘም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ድሬ ኢንዱሰትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር 300 ሺህ ብር፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 የነገ ሰው ጽዳት ድረጅት 300 ሺህ ብር እና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ሰንሴት ሆምስ ድርጅት 300 ሺህ ብር ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡
ባለስልጣኑ በዛሬው እለት በአጠቃላይ 2 ሚሊየን 600 መቶ ሺህ ብር ቅጣት መቅጣቱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኮሙኔኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።