AMN – ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የውጭ አጀንዳዎችን ከመድገም ተላቀው፣ ትኩረታቸውን በሀገር በቀል እውቀቶች፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በሀገራዊ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሚዲያ እመርታ ለትርክት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሄደዋል።
በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የሚዲያ ተቋማት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በሚቀይሩና መፍትሔ አመላካች በሆኑ የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል።
በተለይም በምርትና በገበያ መካከል ያለውን ሰፊ የዋጋ ልዩነት በመተንተን ረገድ የሚታየውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት፣ ማኅበረሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጥ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ከሚዲያው እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

በበለጸጉ ሀገራት ንግድና ፈጠራ ዋነኛ የሚዲያ አጀንዳ ባይሆኑም ለኢትዮጵያ ግን እነዚህ ጉዳዮች የህልውና መሠረት መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሚዲያው ከወቅታዊ የፖለቲካ ትርክቶች ባለፈ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ በሆኑ የፈጠራ ሥራዎችና በንግድ ሥርዓቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የዘመኑን የቴክኖሎጂ ሽግግር ተከትሎ ሚዲያው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሥራው ላይ ማዋል እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ወጪን ለመቀነስና የሥራ ውጤታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል፣ የሚዲያ ባለሙያነት ከከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሐሰተኛ መረጃዎች የሚነግዱ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ሊጠናከርና ሙያዊ ሥነ-ምግባር ሊከበር እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሚዲያ ከሀገር ውስጥ አልፎ “የአፍሪካ ድምፅ” የመሆን ራዕይ ሊኖረው እንደሚገባ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በአረብኛና በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የሚደረጉ ስርጭቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ሚዲያው አህጉራዊ ተፅዕኖውን እንዲያሳድግ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌቻቸው