የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ አቅም በማጠናከር የአፍሪካን ድምፅ በዓለም መድረክ ከፍ ማድረግ!!

You are currently viewing የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ አቅም በማጠናከር የአፍሪካን ድምፅ በዓለም መድረክ ከፍ ማድረግ!!

መንግስት በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ እና ተገቢውን ስፍራ እንድታገኝ የሚያስችሉ ስልታዊ አቅጣጫዎችን ነድፎ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ። መንግስት የሚከተለው የውጭ ግንኙነት መርህ በዋናነት “በጋራ ተጠቃሚነት” ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ በተለይም አፍሪካን በሚመለከቱ ጉዳዮች “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚለውን ፅኑ አቋም በመከተል የአህጉሪቱን አንድነትና ውህደት ለማጠናከር ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

መንግስት ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያን የአህጉራዊ ውህደት ማዕከል ለማድረግ በወሰዳቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል ። በዚህም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት እንዲተገበርና የአፍሪካ ህብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪና ጠንካራ ድርጅት እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከዚህ ባለፈም አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሚገባትን ፍትሃዊ ውክልና እና ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ግፊት በላቀ ደረጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ። ይህም ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ድምፅ ሆና የመቆም ታሪካዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት ያላትን ዝግጁነት ያሳያል።

ከሌሎች አህጉራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ፣ መንግስት ስልታዊ አጋርነትን መሰረት ያደረገ ዘርፈ ብዙ ትብብር እየገነባ ይገኛል። ከአሜሪካ ጋር በሰላምና ደኅንነት፣ ከአውሮፓ ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅና እስያ ሀገራት ጋር በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ተደርጓል። በተለይም ከመካከለኛው ምስራቅና እስያ ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ግንኙነት በማጠናከር ለኢንደስትሪ ፋሲሊቲዎች ግንባታ፣ ለማሪታይም ደኅንነትና ለሽብርተኝነት መከላከል ምቹ መደላደል ለመፍጠር በንቃት እየተሰራ ነው። እነዚህ ጥረቶች ለኢትዮጵያ ምርቶች ሰፊ የውጭ ገበያ ከመፍጠራቸውም በላይ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ያስገኙ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ችለዋል። በተጨማሪም በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ዜጎች መብትና ጥቅማቸው እንዲከበር በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ።

የመንግስት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችም የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ ክንድ ይበልጥ ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ናቸው። በጤና፣ በትምህርት፣ በጠፈር ሳይንስ፣ በኒውክሊየር ኃይል ለልማት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፎች የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ትብብሮች ወደ ተጨባጭ ምርትና አገልግሎት እንዲቀየሩ በትኩረት ይሰራል። የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን በእጥፍ በማሳደግ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ የሚያሳድጉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት መታቀዱም ተገልጿል። ይህም ሀገራዊ የልማት ፍላጎቶችን ማዕከል ያደረገ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን የሚያጠናክር ሲሆን፣ የዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሳኩ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ያጎለብታል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ዲፕሎማሲያዊ ድል ጀምሮ እስከ ቀጠናዊ የሰላም ግንባታ ሚናዎች የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌትነት ለማሸጋገር መሠረት ናቸው ። ኢትዮጵያ በአህጉራዊ አንድነትና በዓለም አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የምትገነባው ይህ ዲፕሎማሲ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚያስከብር፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የአፍሪካዊነት ኩራትን በዓለም መድረክ ከፍ የሚያደርግ የሁለንተናዊ ብለጽግና መደላድል ነው ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review