በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በፖለቲካዊ አካሄድ ጤናማነት ላይ መነጋገር፣ መደማመጥ እና ሀሳቦችን ማዋጣት ያንንም ደግሞ ለመተግበር በጋራ መትጋት ወደፊትም መጠናከር ይገባዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከአዲስ አበባ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርበን የመሥራት ባሕልን እየገነባን ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡
የእርስ በርስ መደማመጥ እና የመመካከር ባሕልን በማዳበር ለጋራ ሀገር ግንባታ በትብብር የመሥራት ልምድ ሊጠናከር ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ውይይቱ “ለተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት እና ባሕል ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን፣ የውይይቱ ተሳታፊ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር ልማቶች የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የኮሪደር ልማት፣ ህፃናትን መመገብ እና ሳቢና ማራኪ አካባቢዎችን መፍጠር ላይ የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በከተማዋ ብሎም በሀገር ዘላቂ ሰላምን ማስፈን፣ ብልሹ አሰራር እና የኑሮ ውድነት ጉዳይ ትኩረት ቢሰጣቸው እና ቢስተካከሉ ብለው ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ዘላቂ ሰላምን በከተማዋ እና በሀገሪቱ ለማምጣት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተጀመረው ልምድም ቢዳብር መልካም ነው ሲሉ አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከለውጡ ወዲህ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ በገዢው ፓርቲ እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው የፖለቲካ እሳቤ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሀገራዊ እና በከተማ አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተግባቦት በመፍጠር ተቀራርቦ የመሥራት ባሕል እየተገነባ መሆኑን አመላክተዋል።
አዲስ የፖለቲካ ባሕልን በተጨባጭ እየገነባን እንገኛለን ያሉት ከንቲባዋ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን ለመጨበጥ በሕዝብ ይሁንታ ምርጫን ማሸነፍ እንዳለባቸው የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ ብልጽግና ሥልጣን ከያዘ በኋላ አዲስ እና የላቀ የፖለቲካ ባሕል መለማመድ አለብን ከሚል ቁርጠኛ አቋም የተነሳ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ ጭምር እንዲካተቱ ተደርገው አብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የከተማ አሥተዳደሩ የነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል ላከናወናቸው በርካታ የልማት ሥራዎች ማበረታታት መቻላቸው በጎ የዴሞክራሲ ልምምድ እንደሆነም ገልጸዋል።
እንደ ከተማ አሥተዳደር የተጀመሩ አዎንታዊ መስተጋብሮች እና የሕዝቡን ፍላጎቶች መሠረት ያደረጉ ተግባራት በፍጥነት እና በጥራት የመሥራቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በታምራት ቢሻው