AMN- ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2026 የ-APEX የመንገደኞች ምርጫ ሽልማት (APEX Passenger Choice Awards) “የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ” ሆኖ ተመርጧል፡፡
ይህም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የጉዞ አውታረ መረብ ውስጥ መንገደኞች የሚሰጡትን እምነት እና ታማኝነት የሚያንጸባርቅ ነው።
ሽልማቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች በረራ ካስያዙበት ቅጽበት ጀምሮ መድረሻቸው እስኪደርሱ ድረስ ምቹ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የጉዞ ተሞክሮ ለማቅረብ የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ያሳያል።

ወጥ የሆነ ጠንካራ አገልግሎት፣ የአውሮፕላን ውስጥ ምቾት እና የሥራ ክንውን አስተማማኝነት የመንገደኞችን ፍላጎት ለማርካት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የ-APEX የመንገደኞች ምርጫ ሽልማት በገለልተኛ አካል በተረጋገጠ የደንበኞች አስተያየት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ውጤቱም ሙሉ በሙሉ በመንገደኞች እውነተኛ የጉዞ ተሞክሮ የተቀረጸ ነው። ይህም ሽልማቱን ከመንገደኞች የተሰጠ እውነተኛ የእምነት ድምፅ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ-APEX ደጋግሞ ዕውቅና ማግኘቱ ለአገልግሎት ጥራት እና ለሥራ ክንውን ብቃት ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት ያሳያል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ ሽልማቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት፣ “ይህን እውቅና ከራሳቸው ከመንገደኞቻችን ማግኘታችን ሽልማቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
“የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ” ተብሎ መመረጣችን፣ የአገልግሎት ደረጃችንን ይበልጥ እንድናሻሽል እንዲሁም ደንበኞቻችን የሚተማመኑበትንና የሚደሰቱበትን አገልግሎት እንድንሰጥ ያበረታታናል ሲሉ መግለፃቸውን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።