AMN ሚያዝያ 21/ 2018 ዓ.ም
የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ዛሬም ሲቀጥል አትሌቲኮ ማድሪድ በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ አርሰናልን ምሽት 4 ሰዓት ላይ ያስተናግዳል፡፡
አትሌቲኮ ማድሪድ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰው በሩብ ፍፃሜው ከሀገሩ ክለብ ባርሰሎና ጋር ተፋልሞ ነው፡፡ በድራማ የታጀቡት የሁለቱ ክለቦች የሩብ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን አትሎቲኮ በድምር ውጤት 3ለ2 በመርታት ለዛሬው ጨዋታ በቅቷል፡፡ አርሰናል በአንፃሩ የፖርቹጋሉን ክለብ ስፖርቲንግ ሊዝበንን በድምር ውጤት 1ለ0 በማሸነፍ ነው የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚነቱን እውን ያደረገው፡፡
አትሌቲኮ ከዓመታት በፊት እንደሚወራለት በብርቱ መከላከሉ ብቻ የሚተማመን አይደለም፡፡ ዲያጎ ሲሞኔ ይበልጥ ለማጥቃቱ ትኩረት የሚሰጥ ቡድን ገንብቷል። ለዚህ ማሳያ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች 34 ግቦችን ማስመዝገቡ ነው፡፡ የግብ ብዛቱ ለክለቡ አዲስ ታሪክ ሆኗል፡፡

በዘንድሮ የውድድር ዓመት በተናጥል 38 ግቦችን ካስቆጠሩት ፓሪሰን ዠርማ እና ባየርን ሙኒክ ቀጥሎ የሚጠራ ክለብ እንዲሆንም አድርጎታል፡፡
የዲያጎ ሲሞኔ ቡድን ግማሽ ፍፃሜ ሲደርስ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ ሲሆን ፤ ከዚህ ቀደም ፍፃሜ ለመድረስ ባደረጋቸው ስድስት ፍልሚያዎች በሦስቱ እጅ ሲሰጥ በሦስቱ ተሳክቶለታል፡፡ እስካሁን ግን የተመኘውን ዋንጫ ማንሳት አልቻለም፡፡
አትሌቲኮ ማድሪድ በአውሮፓ ውድድሮች ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ሲገናኝ ጥሩ ክብረወሰን አለው፡፡ ከዚህ ቀደም በ15 የጥሎ ማለፍ የአውሮፓ ውድድሮች ላይ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ተፋጦ 11 ጊዜ በበላይነት አጠናቋል፡፡
አርሰናል አስደናቂ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ይገኛል፡፡ በውድድር ዓመቱ ብቸኛ ሽንፈት ያልገጠመው አርሰናል ካደረጋቸው 12 ጨዋታዎች በ10ሩ ድል ሲያጣጥም ፤ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል፡፡ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከ12 ጨዋታዎች ግብ የተቆጠረበት በአምስቱ ብቻ ነው፡፡

የእንግሊዙ ክለብ በአውሮፓ ትልቁ መድረክ ላይ ለግማሽ ፍፃሜ ሲቀርብ የዘንድሮው ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ሁለቱን ያሳካው በተከታታ ዓመታት ነው፡፡ ይህም በክለቡ አዲስ ታሪክ ሆኖ መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡ አርሰናል ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ሦስት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው አሸንፎ ፍፃሜ መድረስ የቻለው፡፡ ይህም እኤአ በ2005/06 የውድድር ዓመት በአርሰን ቬንገር እየተመራ ቪያሪያልን ያሸነፈበት ነው።
የሚካኤል አርቴታው ቡድን ከስፔን ክለቦች ጋር ከፍ ያለ የበላይነት አለው፡፡ አርሰናል ከስፔን ክለቦች ጋር ባደረገው ሰባት የመጨረሻ የአውሮፓ ውድድር ጨዋታዎች ሁሉንም በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡
ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖን ለማድመቅ የተዘጋጁት ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ ሦስተኛ ዙር ላይ በኤምሬትስ ተገናኝተው አርሰናል 4ለ0 ማሸነፍ ችሎ ነበር፡፡ ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ አራተኛ የአውሮፓ ውድድሮች ግንኙነታቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በጨዋታው በአርሰናል በኩል ሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ኤብሪቼ ኤዜ በስብስቡ ሲካተቱ ፣ ካይ ሃቨርትዝ እና ዩሪየን ቲምበር ግን ከጉዳታቸው ማገገም አልቻሉም።
በሸዋንግዛው ግርማ