በጋዛ የሚገኘው የረድኤት ቡድን በዛቻ ምክንያት ለአንድ ቀን እርዳታ ማቆሙ ተገለጸ

You are currently viewing በጋዛ የሚገኘው የረድኤት ቡድን በዛቻ ምክንያት ለአንድ ቀን እርዳታ ማቆሙ ተገለጸ

AMN – ሰኔ 1/2017 ዓ.ም

በአሜሪካ እና በእስራኤል ይደገፋል በሚል ቅሬታ የሚቀርብበት አወዛጋቢው ሰብአዊ ድርጅት ምንም አይነት የምግብ እርዳታ ከማከፋፈል መታቀቡ ተገልጿል።

ድርጅቱ ዕርዳታውን ማከፋፈል ያቆመው፣ ሃማስ በአካባቢው መስራት እንዳይቻል የሚያደርጉ ዛቻዎች እየሰነዘረ ነው በማለት ሲሆን፣ ሃማስ በበኩሉ ወቀሳውን አስተባብሏል፡፡

ይሁንና በአሜሪካ የግል ደህንነት እና የሎጂስቲክስ ድርጅቶች እንደሚጠቀም የተገለጸው የጋዛ ሰብዓዊ ተቋም፣ በውል ያልዘረዘራቸውን ስጋቶች ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

በዛሬው ዕለትም ሁለት ማዕከላት ዳግም እንደሚከፈቱ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት አስታውቋል።

አንድ የሃማስ ባለሥልጣን፣ ተሰነዘረ ስለሚባለው ዛቻ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መግለጹ ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሃማስ የሚተዳደረው የጋዛ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን ጽሕፈት ቤት፣ የጋዛ ሰብአዊ ድርጅት እንቅስቃሴ በሁሉም ግንባር ሙሉ በሙሉ እንዳልተሳካለት አንስቷል፡፡

ሃማስ በተባበሩት መንግሥታት ለሚመራና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሌላ ሰብዓዊ ድርጅት ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እርዳታ ማቅረብ እንዲችል ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ሁሉም ፍልስጤማውያን ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ተሸከርካሪዎችን እንዲጠብቁ ሃማስ ማሳሰቡን ጠቁሟል።

አሜሪካ እና እስራኤል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሚመራ ሰብአዊ ድርጅት ላይ ሃማስ እርዳታ ይሰርቃል በሚል የከሰሱት ሲሆን፣ የሃማስ ታጣቂዎች ግን ማስተባበላቸውን አር ቲ ኢ በዘገባው አመላክቷል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review