ትራምፕ ለቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ በካናዳ የተገኙ ቢሆንም ስብሰባውን አቋርጠው መውጣታቸው ተሰምቷል።
መሪዎቹ በካናዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 58ኛው የቡድን 7 ሀገራት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በቅንጡዋ የካናዳ ደሴታማ የካናናስኪስ ከተማ ከትመዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚያ እንደደረሱም በፈረንጆቹ 2014 የሩሲያው ፕሬዝዳንት ከቡድን ሰባት እንዲወጡ መደረጋቸው ትልቅ ስህተት ነው ሲሉ ለካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔ ገልፀዋል።
የኢኮኖሚና ፀጥታ ጉዳይን በካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር በአጀንዳነት ለማቅረብ ቢታቀድም በኢራንና እስራኤል ጉዳይ አጀንዳው ሊቀለበስ እንደሚችል የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
የአሜሪካ ታሪፍ ጭማሪ ጉዳይ፣ ማብቂያ ያልተበጀለት የዩክሬን ሩሲያ እንዲሁም ከሰሞኑ የተቀሰቀሰው የኢራንና እስራኤል ግጭት ተባብሶ ባለበት ወቅት ላይ የሚካሄድ በመሆኑ በጉባኤው የራሳቸውንም ሆነ የሀገራቸውን ሚና አጉልተው ማንፀባረቅ ለሚሹት ለአዲሱ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኔይ ነገሮች ቀላል እንደማይሆኑ ይጠበቃል።
በውይይታቸውም በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ላይ በቡድን ሰባት ሀገራቱ መካከል ልዩነቶች መፈጠራቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ውይይቱን ሳይጨርሱ የእስራኤልና ኢራን ግጭት መባባሱን እና አዳዲስ ፍንዳታዎች መደመጣቸውን ተከትሎ መድረኩን አቋርጠው ወጥተዋል።
ትራምፕ የቡድን 7 ሀገራትን ስብስብ አቋርጠው ሲወጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በፈረንጆቹ 2018 በኩቤክ ተካሂዶ በነበረው ስብሰባም የሰሜን ኮሪያውን ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡንን ላገኛቸው እፈልጋለሁ ብለው ውይይቱን ሳይጨርሱ መውጣታቸው ይታወሳል።
እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ካናዳና ጣሊያን ናቸው በዴሞክራሲ የበለፀጉ የቡድን 7 አባል ሀገራት የሚሰኙት።
በማሬ ቃጦ