በአሜሪካ ኬንታኪ ግዛት በዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ላይ በደረሰ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
ትናንት አመሻሽ ላይ በሉዊስቪል ኬንታኪ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የዩፒኤስ የጭነት አውሮፕላን በመነሳት ላይ ሳለ በተከሰተ አደጋ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉን የግዛቱ አስተዳደር ተናግረዋል።
የጭነት አውሮፕላኑ የሉዊስቪል መሐመድ አሊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በመልቀቅ ላይ እንዳለ አደጋው የደረሰ ሲሆን፣ በፍንዳታው ቢያንስ 11 ሰዎች ሳይቆስሉ እንዳልቀረ ተነግሯል።
ክስተቱን ያየ ማንኛውም ሰው አደጋው ምን ያክል አደገኛ እንደሆነ ይገነዘባል ያሉት የኬንታኪ አስተዳደሪ አንዲ ቤሺር፣ የአውሮፕላኑ ሦስት የበረራ ሰራተኞች ከሟቾቹ መካከል ሳይሆኑ እንልቀረ ጠቅሰዋል፡፡
በአደጋው ብዙዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል ባለሥልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።
የበረራ ቁጥሩ 2976 የሆነው የዩፒኤስ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን፣ 144 ሺህ ሊትር ነዳጅ ጭኖ ወደ ሆኖሉሉ ሃዋይ ሊያቀና የነበረ ሲሆን፣ በሉዊስቪል ካለው ማኮብኮቢያ ተንሸራቶ በአቅራቢያው ካሉ ህንፃዎች ጋር መጋጨቱ ተገልጿል።
በአደጋው በተፈጠረ ፍንዳታም የፔትሮሊየም መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ኩባንያን ጨምሮ ቢያንስ ሁለት በአቅራቢያ ያሉ የንግድ ማዕከላትን ማቀጣጠሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
በታምራት ቢሻው