የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ናይጅል ክላርክ ጋር በኢትዮጵያና በድርጅቱ መካከል ባለው የኢኮኖሚ ልማት ትብብር እና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኤ ኤም ኤን በላከው መግለጫ ገልጿል።
በምክትል ዳይሬክተሩ የተመራው ልዑካን ቡድን 2,200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን ጎብኝቷል።
ንጹህና ተመጣጣኝ ኃይል ለማቅረብ እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚያደርጋቸው የለውጥ ጥረቶች አንዱ አካል የሆነውን የግድቡን ግንባታ ዐይን ገላጭ ነው ብለውታል ምክትል ዳይሬክተሩ።
ናይጅል ክላርክ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ልማትና ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገሪቱ በጠንካራ እና የላቀ የኢኮኖሚ መንገድ ላይ እንደምትገኝ ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያገኘቸው የልማት ድጋፍ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቁ የኢኮኖሚ ትብብር መሆኑን የገለጹት አቶ አሕመድ በበኩላቸው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ በማደረጉ ኤክስፖርት እያደገ መሆኑን፣ የዋጋ ግሽበት መቀነሱን፣ የግብርናው ዘርፍ እያደገ መምጣቱን፣ ገቢ መጨመሩን፣ በዕዳ ቅነሳ ረገድ ስኬታማ ውይይት መካሄዱን፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ ማደጉን፣ የቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃቱንና ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል፡፡
ናይጅል ክላርክ “በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የተገኙት አስደናቂ የለውጥና የኢኮኖሚ ውጤቶች ላይ ፍሬያማ ውይይት በማድረጋችን አመስጋኞች ነን” ብለዋል።
ከ18 ወራት በፊት በድርጅቱ ቦርድ የጸደቀው የተራዘመ የብድር ፕሮግራም መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን፣ ሁሉን አቀፍ ዕድገትን ለማምጣት፣ በግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማጎልበትና የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ለማሻሻል ያለመ እንደነበር ተገልጿል።