በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)
መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማብዛትና ማጥራት የሚሉት እሳቤዎች የመደመር መንግሥት ዋነኛ ማጠንጠኛዎች ናቸው፡፡ የእነዚህን እሳቤዎች ምንነት እና አስፈላጊነት የመደመር ፍልስፍና አመንጪ የሆኑት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጽፈው ለንባብ ባበቋቸው “መደመር፣ የመደመር መንገድ፣ የመደመር ትውልድ እና የመደመር መንግሥት” መጽሐፍት በስፋት እና በጥልቀት ተንትነው አቅርበዋል፡፡ በተለያዩ ሠፋፊ መድረኮች ላይም ሃሳቡን ለማስረፅ ጥረዋል፤ አሁንም በዚሁ ትጋታቸው ቀጥለዋል፡፡ እሳቤዎቹን በንድፈ ሃሳባዊ መልኩ ተንትኖ ከማቅረብ እና ከማስረዳት ባሻገር መሬት በነካ ተግባራዊ የሥራ ውጤት አሳይተዋል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ጥልቅ እና ሠፊ ከሆነው የመደመር መንግሥት እሳቤዎች ውስጥ “መፍጠን” የሚለውን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ካለመችው የዕድገት እና የብልፅግና ማማ ላይ ለመድረስ መፍጠን ግዴታዋ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የመፍጠን እሳቤን በተግባር እየገለጡ ለመጓዝ እንዴት ይቻላል? የመፍጠንን እሳቤ ተግባራዊ በማድረግ የሚገኘው ተጠባቂ ውጤት ምንድን ነው? የሚሉ ነጥቦችን በማንሳት ከመደመር መንግሥት መጽሐፍ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በመጽሐፉ ፀሐፊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀረቡ ገለፃዎች እንዲሁም በጽሑፉ ላይ ምሁራዊ እይታቸውን ያጋሩንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሠላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ሃሳብ በማከል እንመለከታለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የመደመር መንግሥት” በተሰኘው መጽሐፋቸው፤ ኢትዮጵያ ያለባትን የልማት ክፍተት ለመድፈን እና ብልጽግናን ለማምጣት የመፍጠርን፣ የመፍጠንን (ፍጥነትን)፣ የማብዛትን እና የማጥራትን እሳቤዎች እንደ ቁልፍ ስልቶች መጠቀም እንደሚገባት አፅንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡ መጽሐፉ ኢትዮጵያ ያለባትን የድህነት አዙሪት ለመስበር እና የዓለም ተምሳሌት ለመሆን ከባህላዊ አቀራረቦች ወጥታ፣ በእነዚህ አራት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ እና ተጨባጭ የሥራ መመሪያ (blueprint) እንደሚያስፈልጋት ይተነትናል፡፡
ከእነዚህ አራት መሰረታዊ እሳቤዎች መካከል አንዱ የሆነው መፍጠን (ፍጥነት) (Speed/Acceleration): በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ውስጥ በስፋት እና በጥልቀት ተተንትኗል፡፡ ጭብጡም፤ እጅግ በፈጠነው ዓለም አቀፍ ዑደት ውስጥ የኢትዮጵያን አዝጋሚ እንቅስቃሴ አይጠብቁም። በመሆኑም ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ የዕድገት እና ብልፅግና ጉዞ በተፎካካሪነት ለመሳተፍ በዘርፈ ብዙ የልማት መስኮች በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባት። ለዚህ ደግሞ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ “ዛሬ” ላይ በማተኮር ብቻ ወደፊት መገስገስ እንደሚያስፈልግ የሚገልፅ ነው፡፡
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ዋነኛ ጭብጥ የፍጥነትና የፈጠራ ፍኖት ማብራራት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያየ ወቅት አብራርተዋል። በመጽሐፉ የመፍትሔ ፍለጋ ቀጣይ ጥረት ሌላኛው ውልደት መሆኑንም ደጋግመው ጠቁመዋል። “ፍጥነታችን መስፈንጠር አለብን ብሎ ያምናል፡፡ የተከማቸብን ችግር በቀላል ፍጥነት ብቻ የሚገታ አይደለም። የትላንቱን ችግር ለመፍታት ስንጥር የዛሬው ይቀረናል፣ የዛሬውን ልንፈታ ስንል የነገው ይደርሰናል። ለዚህ ነው ፍጥነታችን መስፈንጠር እንደሆነ የምናምነው።” በማለትም የፍጥነት እሳቤን አስፈላጊነት በመጽሐፉ ገፅ 24 ላይ አስፍረዋል፡፡

ፍጥነት እና ፈጠራ የሚሉት እሳቤዎች ለሀገር ዕድገት እና ብልፅግና ቁልፍ መሣሪያዎች ስለመሆናቸው በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ምርቃት መርሃ ግብር በተዘጋጀ መድረክ ላይ ስለመጽሐፉ ትንታኔ ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ እንዳብራሩት፤ የመደመር መንግሥት እንዴት ወደኋላ ቀረን? ከዓለም ጋር የቱ ጋር ተላለፍን? ለሚሉ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ እና መፍትሔ ይዟል፡፡ ከኋላቀርነት በመላቀቅ ዓለም የደረሰበት ደረጃ እንዴት መድረስ እንዳለብን አመላክቷል፡፡ በየዘርፉ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን መፍጠር፤ እነዚህን የፈጠራ ውጤቶች ደግሞ በፍጥነት ወደ ሥራ ማስገባት እና እንደአስፈላጊነቱ ደግሞ የዝላይ ስልቶችን በመከተል የሀገራችንን ብልጽግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ዋነኛ ኃላፊነቱ እንደሆነም በመጽሐፉ ተዘርዝሯል፡፡ የመደመር እሳቤን በመተግበር እና በመደመር ላይ የተቃኘ መንግሥትን በመመስረት ሀገራችንን ወደነበረችበት የኢኮኖሚ እና የስልጣኔ ከፍታ መመለስ፤ ሕዝባችንን ደግሞ ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማሸጋገር ስለመሆኑም አሳይቷል፡፡
በሦስት ክፍሎች፣ በ13 ምዕራፎች እና በ78 ርዕሰ ጉዳዮች የተዋቀረው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ እነዚህን አራት መሰረታዊ እሳቤዎች (መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማብዛት እና ማጥራት) መሰረት በማድረግ ሁለገብ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ክንውኖችን ሁኔታ ከመሰረቱ ዳስሷል። መነሻውም የኋላ ታሪካችን ነው። የት ነበርን? የሚለው ከነትርክቱ ጭምር ተዳስሷል። በዚህም የቀደመው ዘመን ጥንካሬዎቻችን ምን ነበሩ? ድክመቶቻችንስ? የሚሉ ሀሳቦችን በስፋት አንስቷል።
“የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ውስጥ የጠቀሷቸው በርካታ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን፤ በመሰረታዊነት በሦስት አንኳር ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሆኖ አገኘዋለሁ” የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)፤ እነዚህን አንኳር ነጥቦች ያብራራሉ፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ የመጀመሪያው የመደመር መንግሥት አንኳር ነጥብ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ምንነት ላይ ያጠነጠነው ነው፡፡ ትላንትና ምን ነበርን?፣ ዛሬስ የት ነው ያለነው?፣ ነገ ምን ሊሆን ይችላል?፣ ታሪካችን፣ ፖለቲካችን፣ ኢኮኖሚያችን ያለፈበትን፣ አሁን ያለበትንና የቀጣይ መዳረሻው የሚተነተንበት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፤ በዓለም ማዕቀፍ ውስጥ ኢትዮጵያን የተመለከቱበት ነው። ዓለም መቼ ነው ያደገው?፣ ዓለም የኢንዱስትሪ አብዮትን ሲያከናውን እኛ ምን ሆንን?፣ ከዓለም ፈጣን ዕድገት ውስጥ እኛ ተነጥለን እንዴት ነው የዘገየነው?፣ የቱጋ ነው የተዘናጋነው?፣ ለምንስ ነው የተዘናጋነው?፣ እንዴትስ ተንሸራተን ጠፋን? የሚሉት ሃሳቦች የተተነተኑበት ነው፡፡ የጊዜ ታላቅነት የተዳሰሰበት በሦስተኛነት ይጠቀሳል፡፡ በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ውስጥ የጊዜ ታላቅነት (አስፈላጊነት) አጽንኦት ተሰጥቶት እንመለከታለን፡፡ በዚህ ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች በጊዜ መመለስ፣ ከዓለም ጋር ለመወዳደር አቅም መፍጠር፣ ለመቅደም መፎካከር የሚሉት በጥልቀት ተተንትነዋል፡፡ የመሸጋገሪያ መንገዱ ምን መሆን እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡ ለምሳሌ ይዘን የመጣነው የሥራ ባህል፣ ሥራዎችን የመራንበት መንገድ፣ ውጤቱን የመዘንንበት ሂደትን በመቃኘት፤ ከዚህ ሁሉ የተወሳሰበ ችግር ለመውጣት እያንዳንዱን ሥራ በፍጥነት፣ በፈጠራ እና የውድድር መንፈስን በተከተለ አግባብ መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

“ሥራዎችን ከጊዜና ከወቅት ጋር አቀናጅቶ በፍጥነት እና በጥራት መተግበር ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል፤ በመጽሐፍታቸው ላይ አስፍረዋቸው እንመለከታለን” በማለት ምሁራዊ ዕይታቸውን ያካፈሉን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ጥያቄዎች በጊዜና በተገቢው መመለስ እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው መግለጻቸውን፣ ለዚህ ደግሞ የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በቀዳሚነት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ የሀገራችን እጣ ፈንታ በልጆቿ እጅ ላይ እንደሆነ መጠቆማቸውን አብራርተዋል፡፡
ይህንን በተመለከተ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር ትውልድ መጽሐፋቸው ክፍል ሦስት ምዕራፍ ሰባት ላይ፤ ‘እኛ ኢትዮጵያዊያን አሁን ላለንበት የድህነት አዙሪት ዋናው ማሳያችን ጊዜውን ያገናዘበ መፍትሔ ባለመስጠታችን የተጋፈጥነው ጦስ ነው፡፡ ይህም ጦርነት ነው፡፡ የእርስ በእርስ ግጭት ነው፡፡’ ይሉና፤ ይህንን ለማስቀረት ‘ከችግሮቻችን ለመላቀቅ መፍጠን አለብን፡፡ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠርና መጠቀም ይገባናል፡፡ ዓለም ጥሎን ብዙ ርቆ ሄዷል፡፡ ዓለም በሚጓዘው ፍጥነት መሄድ ከባድ ይሆንብናል፡፡ በዚህ ጊዜ ዓለም የተጓዘባቸውን የዕድገት ሂደት ደረጃዎች መከተል አይጠበቅም፡፡ አንዳንዶቹን በመዝለል ወደፊት መገስገስ አስፈላጊ ይሆናል” በሚል መግለፃቸውን ሙሉጌታ(ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
“የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ከቁጭት የሚነሳ ነው፡፡ ዓለም በዚህ ፍጥነት እና በዚህ ደረጃ ሲያድግ ‘ኢትዮጵያ ለምን ወደ ኋላ ቀረች’ የሚለውን ቁጭት አዘል ጥያቄ ያነሳል፡፡ የችግሮቹ አስኳል ከአስተሳሰብ ጉድለት የመነጨ እንደሆነም ያስቀምጣል፡፡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ያመላክታል” በማለት ምሁራዊ ዕይታቸውን ያካፈሉን ሙሉጌታ(ዶ/ር) መፍጠን ለኢትዮጵያ ግድ እንዲሆን ያደረገው ምክንያትን አብራርተዋል፡፡
እንደሳቸው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የመፍጠን እሳቤን ተግባራዊ እንድታደርግ አሰገዳጅ ከሆኑ ምክንያቶች ዋነኛው ዓለም ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ዓለም በከፍተኛ የዕድገት ግስጋሴ ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ የቴክኖሎጂ ልህቀት ከፍታው ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) ደረጃ የደረሰበት ነው፡፡ እንደ ውቅያኖስ ሰፊ እና ጥልቅ በሆነው ዓለም ውስጥ ቆሞ መጠበቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ቆሞ የጠበቀ በውቅያኖሱ ይሰምጣል፤ ይጠፋልም። ስለዚህ እኛ ከቀሪው ዓለም ጋር ለመወዳደር እና ለመፎካከር፤ ለዘመናት ወደ ኋላ የቀረንባቸውን ጊዜያት ቁጭትን በሚያካክስ መልኩ ለመከወን እጅግ በጣም መፍጠን ይጠበቅብናል፡፡ ለምሳሌ የሥራ ባህላችን ላይ መፍጠን የሚለውን መርህ በአግባቡ መተግበር ይገባናል፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ይገባናል፡፡ ብዝሃ ኢኮኖሚ ትግበራን አጠናክሮ መተግበር አለብን። ግብርናን፣ ቱሪዝምን፣ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን፣ ማዕድንን፣ ኢንዱስትሪውንና ሌሎችን የኢኮኖሚ ዘርፎች በጥናት ላይ በተመሰረተ አግባብ ለፈጣን የሀገር ዕድገትና ብልፅግና ጥቅም ላይ የማዋሉ ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
አያይዘውም፤ “መፍጠን የሚለውን እሳቤ እንዴት መተግበር እንችላለን?” ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤“የኛ ዕድገት በጣም የዘገየ፣ መሀል ላይም ተንሸራተን የጠፋንበት ወቅት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በፈጣኑ እና በውስብስቡ የዓለም ዕድገት ግስጋሴ ውስጥ ተወዳዳሪ እና ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት ተግባራትን በፍጥነትና በውጤታማነት ማከናወን ግድ ይላል፡፡ ፍጥነታችን በፈጠራ እና በዓላማ የተደገፈ መሆን አለበት፡፡
ፍጥነታችን አንዳንዴ የዝላይ አካሄድንም የሚጠይቅበት ጊዜና ሁኔታ ይኖራል፡፡ ለምሳሌ አውሮፓዊያን አሁን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ላይ ለመገኘት ብዙ መቶ ዓመታትን አልፈዋል፡፡ እኛ እነሱ የደረሱበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መቶ ዓመታትን መጠበቅ አይኖርብንም። በሃያ፣ በአሥር እና ከዚያም ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማሳካት መዘለል ያለባቸውን የዕድገት ሂደት ደረጃዎች መዝለል ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያሉንን ሃብቶች ለይቶ ማወቅ እና በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ወሳኝ ነው” የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)፣ የመፍጠንን እሳቤ ከሀገራዊ ቁልፍ አጀንዳዎች ጋር በማስተሳሰር በሰጡት ማብራሪያ፤ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበሩበትን በርካታ ጫናዎች በመቋቋም ለማጠናቀቅ እና ጥቅም ላይ ለማዋል የተሄደበት መንገድ እንደ ሀገር ለተያዘው የመፍጠን መርህ በማሳያነት የሚጠቀስ ስለመሆኑ ምሁሩ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ለዓመታት ያለባህር በር እንድትቆይ ያደረጋትን እና ከቀይ ባሕር ጫፍ ገፍቶ ያራቃትን ችግር ለመቅረፍ የምታደርገው የዲፕሎማሲና ተያያዥ የመፍትሔ ጉዞ መፍጠን ይኖርበታል፡፡ የባሕር በርን የማግኘት ጉዳይ በመፍጠን ብቻ ሳይሆን፤ አንዳንድ ሂደቶችን ዘለን ማለፍ ሁሉ ይጠበቅብናል፡፡”
በመጨረሻም ለሀገር ዕድገት እና ብልፅግና ወሳኝ የሆነውን የመደመር መንግስት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ እንዲቻል መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ መሰረት፤ የመደመር መንግሥት እና ከዚያ በፊት ለንባብ የበቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መጽሐፍትን ማንበብ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ይህንን የምለው ለፖለቲካ ድጋፍ አይደለም፡፡ የሀገራችንን ዘመናት የተሻገረ፣ ጥልቅ እና ውስብስብ ችግር ለመፍታት በመጽሐፍቱ ላይ የተተነተኑ ጥልቅ ሃሳቦች መፍትሔ ይሰጣሉ፡፡ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የመፍትሔ አማራጮችን ያመላክታሉ፡፡ ስለዚህ ማንበብ የሚችል ሁሉ ማንበብ ይኖርበታል፡፡
በተጨማሪም፤ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች በተለያዩ አግባቦች የመጽሐፍቱን ይዘትና ጭብጥ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዘመኑ የፈጠራቸውን የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ይህንን ለመሰለ ሀገራዊ ፋይዳ ላለው ዓላማ ማዋል መለመድ ይኖርበታል፡፡
በርካታ ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው የማህበራዊ እሴት መሰረቶቻችን ላይ ሃሳቦቹ እየተነሱ ውይይቶችን ማካሄድም ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍቱ ለፖሊሲ፣ ለስትራቴጂ መነሻዎች በመሆናቸው፤ የየዘርፉ ምሁራንና ሊሂቃን ከዚህ ዓላማ መጠቀም ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመጽሐፍን ዳሰሳ (ቡክ ሪቪው) መሥራት፣ ፓናል ውይይት የማሰናዳትና ሙግት (ክርክር) የማድረግ … ምሁራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ተቋማት “ወርቃማ ሰኞ” በሚል በሚያሰናዷቸው ሳምንታዊ አጫጭር የውይይት እና የመማማሪያ መድረክ ላይ ከመጽሐፍቱ ጭብጥ መካከል ንዑስ ጉዳዮችን በማንሳትና በመዘጋጀት የወርቃማ ሰኞ መድረካቸው አካልም ማድረግ ይችላሉ፡፡
በደረጀ ታደሰ