የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስጋቱን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሯል -የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስጋቱን ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሯል -የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ

AMN ሚያዝያ 24/2018

የማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የነበረበትን ዘመናት ያስቆጠረ ስጋት በማስወገድ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ መሸጋገሩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር በተለያዩ የሀገራችን ከተሞች ያስገነባቸውን ዘመናዊ ሕንፃዎች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ይህንኑ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ የነበረበትን ዘመናት ያስቆጠረ ስጋት በማስወገድ ወደ ላቀ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

አፈ ጉባኤው እንደገለጹት ተቋሙ ላለፉት ሰባት ዐሥርተ ዓመታት የመንግሥት ሠራተኛው ዋስትና ሆኖ ቢቆይም፣ የጡረታ ፈንዱን በአግባቡ የማንቀሳቀስ እና ወደ ኢንቨስትመንት የመቀየር አቅም ማጣቱ ለረጅም ጊዜ ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የለውጡ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት እና በወሰዳቸው የሪፎርም እርምጃዎች አዳዲስ አዋጆች እና የአስተዳደር ደንቦች እንዲጸድቁ ተደርጓል።

ይህም ተቋሙ የነበረበትን ስጋት ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ፈንዱን ከማስጠበቅ ባለፈ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማራ እና በሀገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለውም፣ ዛሬ የተመረቁት ዘመናዊ ሕንፃዎች ከግዙፍ ቁሳዊ ሀብትነታቸው ባሻገር ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ እና የነገው ብሩህ ተስፋ ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ሕንፃዎቹ የተገነቡት ከድንጋይ እና ከብረት ብቻ አይደለም፤ በእያንዳንዱ ጡብ ውስጥ የጡረታ ባለመብቶች ክብር፣ የሠራተኞች ላብ እና የሀገራችን ተስፋ ታትሞባቸዋል” ሲሉ የምረቃው ዋና ዓላማ የባለመብቶችን ክብር እና እርካታ ማረጋገጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለወደፊቱም የፈንዱን ዘላቂነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋፋት እና አገልግሎቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ረገድ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመልክቷል።

አፈ-ጉባኤው መንግሥት ለተቋሙ የሚያደርገው ድጋፍ ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል በመግባት ለስኬቱ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review