AMN – ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የወተት ምርቶችን ለከተማዋና በመላው ሃገሪቱ ለተጠቃሚዎች በስፋት ለማቅረብ ነባሩን የላሜ ዴይሪ አምራች ኢንዱስትሪ ተደራሽነትን የሚያሰፋ ተጨማሪ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መርቀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ዛሬ በግሉ ዘርፍ አግሮ ኢንዱስትሪ የወተት ምርቶች በማቀነባበር በምርት አይነት፣ በብዛት እና ጥራት የወተት እና የወተት ምርቶችን ለከተማችንና በመላው ሃገሪቱ ለተጠቃሚዎች በስፋት ለማቅረብ ነባሩን የላሜ ዴይሪ አምራች ኢንዱስትሪ ተደራሽነቱን የሚያሰፋ ተጨማሪ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ መርቀናል ብለዋል።

ሃገራችን በርካታ የቀንድ ሃብት ያላት ቢሆንም በእሴት ሰንሰለት እና በምርታማነት ውስንነት ምክንያት የወተት አቅርቦቱ ላይ አሁንም እጥረት ያለበት መሆኑ ይታወቃል ሲሉም ገልጸዋል።
ይሄ ደግሞ ወተት እያገኙ ማደግ የሚገባቸውን ህጻናትና አምራቹን ዜጋ የሚጎዳ ነው ያሉት ከንቲባዋ ዛሬ በላሜ ዴይሪ ያየነው በምርት ብዛት እና አይነት በዘመናዊ መንገድ ጤናማ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የወተት ምርቶች ማምረት መጀመሩ ችግሩን የሚያቃልል ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለአርሶ አደሮቻችንም ያመረቱትን ምርት ለገበያ በጥራት ማቅረብ እንዲችሉ የገበያ ትስስር የመፍጠር ጥሩ ጅማሮ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።