አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መዲናዋ በፀረ ሙስና እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ባበረከተው አስተዋፅኦ እውቅና አግኝቷል
መንግስታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በማድረግና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይህንን ያሉት ትናንት 22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረበት ወቅት ነው፡፡
መንግስታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን በማድረግና ተጠያቂነትን በማስፈን ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እና ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች እንደሚጠናከሩ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ ሂደቱ የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሕብረተሰቡን ከፍተኛ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ ወይዘሮ አዳች አክለውም ቤተሰብ፣ ማህበረሰቡ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት ወዘተ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የፀረ ሙስና ትግላችን ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ከንቲባዋ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግናችን ፀር፣ የኢፍትሐዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል ብለዋል።
በዚህም እንደ ሀገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግስትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ በማዋላችን አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ችለናል ሲሉ አክለዋል፡፡
22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ስርዓታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ብንችልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ኃላፊዎች እና ሰራተኞች የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉበኝነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም፣ ሙስና ፀያፍ የሆነ፣ የሀገርን ገፅታ የሚገታ፣ ትውልድን የሚጎዳ እና ኢ-ፍትሐዊነትን የሚያነግስ ተግባር በመሆኑ የመላው ማህበረሰብን እና የሁሉንም ተቋማት ትግል የሚጠይቅ ቀዳሚ ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በየዘመናቱ በነበሩ የየስርዓቱ መሪዎች የሀገር ሀብት ወደ ውጪ በማሸሽና በማከማቸት፣ ከባለሃብቶች ጋር ከሀገር ውጪ በመስራት የሀገራችንን ልማት እና እድገት የሚያቀጭጭ ተግባር በዚህ ዘመን ታሪክ ሆኖ አልፏል ብለዋል፡፡
ይህን ጅምር ስራ የበለጠ ለማጠናከር በእያንዳንዱ ስራችን ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ በማፍራት ረገድ ኃላፊነት ያለብን ተቋማት አቅደን መስራት እና ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ የሀሳብና የተግባር አንድነቱን በማፅናት በግለሰቦች ደረጃ ሳይቀር በመንግስት ኃላፊዎችና በሠራተኞች የሚታዩ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች ላይ ሁላችንም እጅለ ለእጅ ተያይዘን መስራት እና ትውልድ ላይ የሞራል ልዕልና እንዲበለፅግ ስር የሰደደውን ኢፍትሐዊ አካሄድ መዋጋት ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡
የበለጠ የፀረሙስና ትግሉን በማጠናከር ተጠያቂነትን ለማስፈን ቃል የምንገባበትና የገባነውን ቃል የምናድስበት ስለሆነ ኃላፊነታችንን በአግባቡ በመወጣት፣ አሰራራችንን ግልፅ በማድረግ፣ ከሰው ንክኪ ነፃ ሆነን ህዝባችንን እናገልግል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረጂ በዕለቱ በአቀረቡት ፅሑፍ፣ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን አመላክተዋል፡፡
በለውጡ ዓመታት ውስጥ 10 ከቢሊዮን ብር በላይ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ማዳን መቻሉን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ 73 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከ100 ሺህ በላይ አመራሮች፣ ፈፃሚዎች እና ደላላዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የአዲስ አበባ ከተማ ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 22ኛውን የፀረ ሙስና ቀን ባከበረበት ዕለት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እውቅና አግኝቷል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መዲናዋ በፀረ ሙስና እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ባከናወነችው ውጤታማ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አበርክቶው ላቅ ያለ እንደነበርም ተገልጿል። ተቋሙ ብልሹ አሰራርን የሚያጋልጡ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ወደ ህዝብ እያደረሰ እንዳለም ተገልጿል።
የፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከአሁን ቀደም ባዘጋጀው የእውቅና መርሃ ግብር ላይ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ ሙስናን እና ብልሹ አሰራሮችን ከመከላከል አንፃር ከፍተኛ አበርክቶ ለነበራቸው ሶስት የሚዲያ ተቋማት እውቅና መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በመለሰ ተሰጋ