የታሪክና የጥበብ ከተማ በሆነቸው፥ የኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ሐውልት በግርማ ሞገስ በቆመባት፣ የያሆዴ በዓል ድምቀትና የሀዲያ ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት መገለጫ በሆነችው ሆሳዕና ከአንድ ቤተሰብ አስገራሚ የልጆች ስያሜ ይገኛል።
መምህር አሸናፊ ታደሰ ይባላሉ – የሶስት ልጆች አባት ናቸው። ለልጆቻቸው ያወጡላቸው አስገራሚ የስም ስያሜ ግን ለሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች መነጋገሪያ ከሆነ ውሎ አድሯል። መምህሩ ለልጆቻቸው ያወጡላቸው ስያሜ ግን ብዙዎቻችን እንደምናደርገው የቤተሰብ መታሰቢያን፣ ሃይማኖታዊ ትርጉምን ወይም የቃላትን ውበት ላይ ተመርኩዘው አይደለም። በአንጻሩ “ስም ማለት የታሪክ ማሕደር፣ የጊዜ መዝገብና የቆሙለት ዓላማ መገለጫ ነው” የሚለው ርዕዮተ ዓለማቸውን እንዲሸከም አድርገው ነው።
መምህር አሸናፊ የታሪክ ሰነድ እንዲሆን ለልጆቻቸው ያወጡላቸው መጠሪያ “መደመር”፣ “ኮሪደር” እና “ብልጽግና” ሆኗል።

ስያሜውን እንዴት ሊያወጡላቸው ቻሉ?
የመጀመሪያ ልጃቸው የተወለደችው ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመስቀል አደባባይ ከተደረገው የመደመር መንግስት የድጋፍ ሰልፍ በኋላ ነበር። እናም “መደመር ለኢትዮጵያ ተስፋ ነው” በሚል እምነት ለበኩር ሴት ልጃቸው መደመር አሸናፊ የሚል ስያሜ ሰጧት።

6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 2013 ዓ.ም. በተካሄደ ማግስት ደግሞ ሁለተኛ ልጃቸው ይህቺን ምድር ሲቀላቀል መምህር አሸናፊም “ብልጽግና ከፓርቲ ስም በላይ ማደግና መለወጥ ነው” በሚል አመክንዮ ብልጽግና ብለው መጠሪያ ለወንድ ልጃቸው አወጡለት።
አዲስ አበባ ላይ ጀምሮ በሀገራችን የተለያዩ ከተሞች የተጀመረውን የኮሪደር ልማትና የከተሞችን ውበት ለመዘከር ሲሉ ደግሞ ሶስተኛዋ ሴት ልጃቸውን ኮሪደር ብለው ጠሯት። የሶስቱም ልጆቻቸው ስያሜ ከራሳቸው ጋር “አሸናፊ” የሚለው ጋር ሲጣመር የመደመር መንግስት ለውጥና ስኬት የሚናገር መሆን ችሏል።

የልጆችን ስም ከወቅታዊ ክስተት ጋር ማገናኘት በኢትዮጵያ ፖለቲካና ታሪክ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ወቅታዊ ክስተቶችን ተከትሎ ስም ማውጣት አዲስ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ያህል በዓድዋ ድል ወቅት “ዓድዋ”፣ “ጣይቱ” እና “ምኒልክ” የሚሉ ስሞች የሀገራዊ ኩራት መገለጫ ሆነው የበርካቶች መጠሪያ ስያሜ ሆነው ትውልድ ተሻግረዋል። በ1960ዎቹና 70ዎቹ የደርግ ዘመን “አብዮት”፣ “ትግል”፣ “ፋኖ”፣ “ቀይ” እና “ለዓለም” የሚሉ ስሞች በብዛት ይወጡ ነበር። ይህን በወቅቱ የነበረው የርዕዮተ-ዓለም ትኩሳት በቤተሰብ ውስጥ ማሳያ ነበር። በተመሳሳይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር “ሕዳሴ” እና “ዓባይ” የሚሉ ስሞች በማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት ተመራጭ ሆነዋል። እነዚህን ስያሜዎች ለልጆቻቸው ያወጡ ወላጆች በድርጊታቸው የሚኮሩትን ያህል ከጊዜ በኋላ ይህን ስያሜ ባላወጣሁላቸው ብለው የሚጸጸቱም እንዳሉ በተለያየ አጋጣሚ ተመልክተናል።
የመምህር አሸናፊን ጉዳይ አስገራሚ የሚያደርገው ግን የዘመኑን ለውጥ በቤታቸው ውስጥ ለመሰነድ ለልጆቻቸው ያወጡትን ስያሜ በተመለከተ ሲጠየቁ “አሁን ላይ መደመር፣ብልጽግና እንዲሁም ኮሪደር ብዬ ያወጣሁላቸውን የልጆቼን ስም መንግስት ቢቀየር እንኳን በፍጹም አልቀይረውም፤ ምክንያቱም እኔ በዓላማዬ የጸናሁ ሰው ነኝ፡፡” ብለዋል። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ እነዚህ ስያሜዎች የልጆቻቸው የቤት ስያሜ ሳይሆኑ የመዝገብ ስማቸው እንዲሆኑ በልደት ምስክር ወረቀታቸው ላይ የሰፈሩ መሆናቸው ነው፡፡

የቤተሰቡ ቀጣዩ ልጅ ስም ማን ይሆን?
“ሀባይም ጡምኒ ዋተኮ” (እንኳን ደህና መጣችሁ) በሚለው የፍቅር ሰላምታ ከምትታወቀው ሆሳዕና ከተማ የበቀሉት መምህር አሸናፊ በሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ባለው ለውጥ በየቀኑ እንደተደመሙ ናቸው። ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸው መምህር አሸናፊ ለልማትና ዕድገት ያላቸው አዎንታዊ አመለካከት እና ለለውጥ ያላቸው ስሜት አሁንም ገና እንደታመቀ ነው።
እና ለሀገራችን የባሕር በርና ሉዓላዊነት ጉዳይ አጀንዳ ስለሆን “ሉዓላዊነት” ይሉት ይሆን? ወይስ የሀገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት እየተደረገ በመሆኑ “ዲጂታል” ይሉታል ብላችሁ ታስባላችሁ? ወይስ ሁሉንም የሚያቅፍ ስም ለመስጠት ፈልገው “ኢትዮጵያዊነት” ይሆን የሚሉት?
እኛ የመሰለንን ግምት ብናስቀምጥም መምህር አሸናፊ ግን ይፋ ባያደርጉልንም አራተኛ ልጅ ቢወልዱ ማን እንደሚሉት ከወዲሁ ስም አዘጋጅተዋል። ስም መለያ ብቻ ሳይሆን የዘመን ምስክርም ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያራምዱት መምህሩ የታሪክ እና ፖለቲካዊ እምነታቸውን በልጆቻቸው ስም ውስጥ መዘከራቸውን በመቀጠል አራተኛው ልጃቸው ሲወለድ ያኔ ደግሞ እንደአዲስ ያስገርሙን ይሆን?
መምህር አሸናፊ ለአራተኛ ልጃቸው ምን ስም ሊያወጡለት ይችላሉ ብለው ይገምታሉ? እናንተስ በዚህ ዘመን በአካባቢያችሁ የወጣ አስገራሚ ስያሜ ገጥሟችሁ ይሆን? ሀሳባችሁን በኮሜንት አጋሩን።
በያለው ጌታነህ