የማንችስተር ዩናይትድ ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ

AMN- ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከጀመረ ሁለት ሳምንት የሆነው ማንችስተር ዩናይትድ ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

የማይክል ካሪክ ቡድን የኖርዌይውን ሮዘንበር ለመግጠም ወደ ስፍራው አቅንቷል።

ማንችስተር ዩናይትድ በመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በሄልሲንኪ አድርጎ ፣ በእንግሊዝ ቻምፒየንሺፕ ተወዳዳሪው ሬክሳም 1ለ0 መሸነፉ ይታወሳል።

ለዛሬው ጨዋታ በስብስቡ ውስጥ ቤንያሚን ሼሽኮ እና ማቲያስ ደሊግት አልተካተቱም። ሼሽኮ በውድድሩ መጨረሻ ከሊቨርፑል ጋር በነበረው ጨዋታ ከገጠመው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ አላገገመም። ስሎቬኒያዊው አጥቂ በክለቡ የልምምድ ማዕከል ካሪግተን በግሉ መስራት ጀምሯል።

ወገቡ ላይ በደረሰበት ጉዳት ለበርካታ ወራት ከሜዳ የራቀው ተከላካዩ ማቲያስ ደሊግትም በጨዋታው አይሳተፍም። ኔዘርላንዳዊው ተከላካይ መቼ ወደ ሜዳ እንደሚመለስም ግልፅ አይታወቅም።

ከአዲስ ፈራሚዎቹ አንድሬ ሳንቶስ ከስብስቡ ጋር አብሮ ተጉዟል። ከቼልሲ የፈረመው የ22 ዓመቱ ብራዚላዊ ከሬክሳም ጋር በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ 45 ደቂቃ ተጫውቶ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርጓል።

ከሊድስ ዩናይትድ የፈረመው ግብ ጠባቂው ካርል ዳርሎው ለጨዋታው ዝግጁ አይደለም። ከአስቶንቪላ ዩናይትድን የተቀላቀለው ዩሪ ቲሊሞንስ በዓለም ዋንጫው በመሳተፉ እረፍት ተሰጥቶታል።

ለጨዋታው ወደ ኖርዌይ ካቀኑት ተጫዋቾች መካከል በርከት ያሉ የአካዳሚ ወጣቶች ይገኙበታል። ዩናይትድ ትልቅ ተስፋ የጣለበት የ15 ዓመቱ ጄጄ ጋብሬል ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ ነው።

ጨዋታው ሮዘንበርግ በሚጠቀምበት ሌርኬንዳል ስታዲየም ምሽት 1:00 ይጀምራል። ማንችስተር ዩናይትድ ከቀናት በፊት ያስተዋወቀው በውድድር ዓመቱ የሚጠቀምበት ሁለተኛ መለያውን እንደሚጠቀም አስታውቋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review