AMN- ሐምሌ16/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አከናውኗል።
ደም በመለገስ የወገኔን ህይወት እታደጋለሁ በሚል መርህ ነው መርሃ ግብሩ የተከናወነው።

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መቅደስ ተስፋዬ ሰብአዊነት እና መልካም ስነ-ምግባር በበጎ አድራጎት ይገለፃሉ ብለዋል።
ሙስናን መታገል ማለት ሌብነትን መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ ሰብአዊነትን ማሳየትና ለወገን ደራሽ መሆንም ጭምር በመሆኑ በዛሬው ዕለት የለገስነው ደም የብዙዎችን ሕይወት ይታደጋል ብለን እናምናለን ሲሉ አብራርተዋል።

በጎነት ለራስ የሚሰጠው የህሊና እርካታ በምንም እንደማይገኝ የገለፁት የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ሠራተኞች ፣ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ የሆነውን ደም መለገስ የውስጥ እርካታን ይሰጣል ብለዋል።
ሠራተኞቹ አክለውም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈው ደም በመስጠታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው፤ ሌሎችም በዚሁ መርሃ ግብር ተሳታፊ በመሆን ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ከ50 በላይ የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ፣ የበርካቶችንም ህይወት ለመታደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተጠቅሷል።
በሚካኤል ህሩይ