AMN ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የጤና ምርመራ ፣ ምክር እና ሕክምና አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ – ግብር አካሂዷል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በያዝነው የክረምት ወቅት እንደ ሀገር ለ20 ሚሊዮን ዜጎች ነጻ የጤና ምርመራ ፣ የምክር እና የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል ሲሉ አንስተው 120 ሺህ ያህሉ ደግሞ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል አግልግሎቱ ይሰጣል ብለዋል ።
በመንግሥት እና በግል ትብብር የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ከፍሎ መታከም ለማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች አበርክቶው የላቀ መሆኑንም ዶክተር መቅደስ አንስተዋል ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት ፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተናበበ እና የተቀናጀ ስራዎች በመስራቱ በጤናው ዘርፍ በጎነት በየቦታው እንዲስፋፋ ሆኗል ብለዋል።
በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት ቅንጅታዊ ስራዎችን ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላልም ብለዋል፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጂ ዶ/ር አብርሃም እሸቱ በዘንድሮው በጎ ፈቃድ ነጻ የጤና የምርመራ ፣ ምክር እና ሕክምና አገልግሎት ላይ ከ 30 በላይ የግል የሕክምና ተቋማት ለማህበረሰቡ አግልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።
ሆስፒታሉ በክረምት በጎ ፈቃድ ነጻ የህክምና አግልግሎት ከ120 ሺ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ማቀዱን ገልጸዋል ።
ከተለመደው ሕክምና በተጨማሪ የስፔሻሊቲ ሕክምና ፣ ሲቲ ስካን እና ኤም አር አይ አገልግሎት የነጻ ጤና ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ዋና ስራ አስኪያጂ ተናግረዋል ።
በዳንኤል መላኩ