የጤና ቱሪዝም ጡቦች

You are currently viewing የጤና ቱሪዝም ጡቦች
  • በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ አዳዲስ እና የነባር ሆስፒታሎች እድሳት የጤና ቱሪዝምን ለማስፋፋት
    የተያዘውን ውጥን እንደሚያግዙ ተጠቁሟል

በዓለም ላይ የጤና ቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን እያሳየ የሚገኝ ዘርፍም ነው። እንደ ቴሌ መድኃኒት፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሮቦቲክስ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ዘርፉ እያደገ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርገው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው። የርቀት ሕክምና አገልግሎትም እየተስፋፋ በመምጣቱ ታካሚዎች ወደ ሌላ ሀገር ከመጓዛቸው በፊት ከውጭ ሀኪሞች ጋር በቪዲዮ መገናኘት፣ የምክር አገልግሎት ማግኘት እና ለቀዶ ጥገናም ሆነ ለሌላ ሕክምና መዘጋጀት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

በጤናው ዘርፍ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሰው በጤና ቱሪዝም ታዋቂ መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል ሕንድ፣ ቱርክ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያ፣ አሜሪካ እና ደቡብ አሜሪካ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የዓለም የጤና ቱሪዝም ማህበር እ.ኤ.አ በ2024 ባወጣው መረጃ መሰረትም በየዓመቱ እስከ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለሕክምና ወደ ሌሎች ሀገራት ይጓዛሉ። የዓለም አቀፉ የሕክምና ቱሪዝም ገበያ በየዓመቱ በአማካኝ በ8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር እያደገ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2024 የገበያው ግምት ከ41 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነበር። ይህ ገቢ እ.ኤ.አ በ2034 ወደ 186 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ተገምቷል።

በዘርፉ ከሚንቀሳቀሰው ከፍተኛ ሀብት ውስጥ በቀዳሚነት ከሚቋደሱ ሀገራት መካከል ደግሞ ሕንድ ትገኝበታለች። እ.ኤ.አ በ2023 ለንባብ የበቃው የግሎባል ሄልዝ አክሪዲቴሽን (Global Healthcare Accreditation) መረጃ እንደሚያሳየው፣ ሕንድ በጤና ቱሪዝም ዘርፍ ዋና ተዋናይ ስትሆን ሀገሪቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ውስብስብ የልብ ቀዶ ጥገና፣ የካንሰር ሕክምና እና የአካል ክፍሎች ንቅለ ተከላ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ትሰጣለች። ለጤና ቱሪስቶች የተመቻቸ የቪዛ አሰራር መኖሩ ብዙ ሰዎች ሕንድን እንዲመርጡ የሚያግዝ ሲሆን፣ በዚህም የጤና ቱሪዝም ዘርፍ የሀገሪቷ ዓመታዊ ገቢ በ2022 ወደ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበር መረጃው ያሳያል።

ጉዳዩን ወደ አህጉረ አፍሪካ መልሰን እንመልከት። የጤና ቱሪዝም በአፍሪካ እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ቢሆንም፣ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲወዳደር ገና በጅምር ላይ ያለ ነው ማለት ይቻላል። ምንም እንኳን አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ከጤና ቱሪዝም ገቢ የሚያገኙ ቢሆንም፣ አፍሪካ በአጠቃላይ ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገራት ለሚጓዙ ዜጎቿ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣለች። የአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ እንደገለጸው፣ አፍሪካ በየዓመቱ ወደ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጤና ቱሪዝም ምክንያት ታወጣለች።

ወደ ኢትዮጵያም መለስ ስንል አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩና በመንግስት ደረጃ ከሚሰሩ ስራዎች ባሻገር የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማሳተፍ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቅርቡ መናገራቸው የሚታወስ ነው። አዲስ አበባ በአፍሪካ ደረጃ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን ያላትን አቅም ለመጠቀምና ደረጃዋን ለማሳደግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና አቅጣጫዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፣ የጤና ቱሪዝምን ከማሳካት አንፃር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ለአብነትም በኮልፌ ቀራንዮ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሁለት አዳዲስ ግዙፍ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታሎች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። እንዲሁም በጥሩነሽ ቤጂንግ፣ በራስ ደስታ፣ በዘውዲቱ እና በሚኒሊክ ሆስፒታሎች የተሰሩ ግዙፍ የማስፋፊያ ስራዎችም ተጠቃሽ ናቸው።

ከንቲባ አዳነች የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል የሕክምና ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት፣ በከተማዋ 28 የጤና ተቋማት ተጠናቅቀው ወደ ስራ መግባት ችለዋል። የዘውዲቱ መታሠቢያ ሆስፒታል ግንባታም ሆስፒታሉን የልህቀት ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊው ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በመዲናዋ በጤናው ዘርፍ ተደራሽነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ጥራትን መሠረት ያደረጉ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል። እንደዚሁም የነባር ሆስፒታሎችን ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን ግንባታ አጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ሆስፒታሎችም እያንዳንዳቸው ከ500 በላይ አልጋዎችን መያዝ የሚችሉ መሆናቸውን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ የጥራት ደረጃቸውም ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን አካባቢ የተገነባው እና ከ511 በላይ አልጋዎች ያሉት ሆስፒታልም፣ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ሊሆን እንደሚችል እና ይህም ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ እውን ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ ማሳያ ናቸው።

እንደዚሁም ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ የዘውዲቱ እና የራስ ደስታ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎችንም በማደስ፣ ግዙፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎች በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ሆስፒታሎች እያንዳንዱ ታካሚ በቂ ኦክሲጅን እንዲያገኝ ለማስቻል ኦክሲጅንን ከማምረት ጀምሮ ሌሎች የሕክምና ግብዓቶችም ተሟልተው መገንባታቸውን ተናግረዋል። የግሉን የጤና ዘርፍ ለማበረታታትም ለጤና ተቋማት ግንባታ የሚውል የመሬት አቅርቦት በመደረጉ ሰፋፊ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል ስምንት አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች በቅርቡ ስራ የሚጀምሩ ሲሆን፣ በአራት ነባር ሆስፒታሎች እና ሌሎች ተጨማሪ ጤና ጣቢያዎች የተቋማቱን አቅም በሚያሳድግ መልኩ ሰፊ እድሳቶች ተሰርተዋል። የአዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታዎች እና የነባሮቹን ደረጃ የማሻሻል ስራ ከተማዋ እየሄደችበት ላለው የጤና ቱሪዝምን የማስፋፋት ውጥን እንደሚያግዙ እሙን ነው።

የአፍሪካ የጤና ልህቀት ማዕከል (Africa CDC) በመዲናዋ መገኘት መዲናዋ የአፍሪካ የጤና ዋና መዲና እንድትሆን ትልቅ ሚና ይጫወታል። አዳዲስ የግልና ግዙፍ የሕክምና መንደሮች ግንባታ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ እየተደረገባቸው ነው። እነዚህ ተቋማት ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የሚታከሙባቸውን እንደ ካንሰር፣ የልብና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ያሉ ሕክምናዎችን እዚሁ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው።

የጤና ቱሪዝም ከሕክምናው ባለፈ የታካሚው የማገገሚያ ጊዜ ምቾት የተሞላበት ያደርጋል። የፓርኮችና የመዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ ከተማዋን ለጎብኚዎች ሳቢ አድርጓታል። የሆቴልና ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍም ለጤና ቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካና ከዓለም ጋር ያለውን ትስስር በመጠቀም “Medical Tourism” ፓኬጆችን ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ዮሐንስ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

አዲስ አበባ በርካታ የሕክምና ኮሌጆችና የምርምር ተቋማት መገኛ በመሆኗ፣ የልዩ ባለሙያዎችን (Specialists) ቁጥር ለማሳደግና ጥራቱን ለመጠበቅ ከውጭ ሀገር የሕክምና ተቋማት ጋር የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ስምምነቶች እየተደረጉ ነው። የአፍሪካ ሕብረትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ፣ በከተማዋ የሚኖሩና ለስብሰባ የሚመጡ ዲፕሎማቶች እዚሁ ሕክምና እንዲያገኙ በማድረግ የጤና ቱሪዝሙን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑ መዲናዋ የሕክምና መዳረሻ ለመሆን እየተጋች ስለመሆኑ ማሳያዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ።

በእርግጥ በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን በመሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በባለሙያዎች ስልጠና ላይ ትልቅ መዋዕለንዋይ ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ። ‘ማፒንግ ዘ ሰስቴይነብል ደቨሎፕመንት ኢን ሄልዝ ቱሪዝም’ (Mapping the Sustainable Development in Health Tourism) የተሰኘ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደሰፈረው አንድ ከተማ የጤና ቱሪዝም ማዕከል (Medical Tourism Hub) ሆናለች ሲባል፣ ከተማዋ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ተጓዦች ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች ማለት ነው።

ምቹ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና የከተማ ትራንስፖርት፣ ለታካሚዎችና ለቤተሰቦቻቸው የሚሆኑ ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎች እንደዚሁም ለሕክምና ለሚመጡ ሰዎች የሚሰጥ ፈጣንና ቀላል የቪዛ አሰጣጥ ሂደት ሊኖር እንደሚገባም ጥናቱ ላይ ሰፍሯል። ጥናታዊ ጽሑፉን ያቀረቡት የዘርፉ ተመራማሪዎች ሆሴ ሉይስ አብራንቴስ እና ሳንድራ ኮስታ እንደሚያብራሩት፣ ሕክምናው ብቻ ሳይሆን፣ ከሕክምና በኋላ ያለው የማገገሚያ ጊዜ በከተማዋ በሚገኙ የመዝናኛ ቦታዎች፣ ስፓዎች (Spas) ወይም የተፈጥሮ መዳረሻዎች እንዲያሳልፍ ይደረጋል። ይህም ከተማዋን የጤና እና የደህንነት (Wellness) ማዕከል ያደርጋታል።

ተመራማሪዎቹ አያይዘው ሲገልፁም አንድ ከተማ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ናት ሲባል፣ ፈውስን ከጉብኝት ጋር አቀናጅታ ለዓለም ገበያ የምታቀርብ፣ በዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና ዝና የምታገኝ ከተማ ትሆናለች ማለት ነው። በተጨማሪም ወደ ውጭ ለሕክምና የሚሄዱ ዜጎችን ቁጥር በመቀነስ የሚባክነውን የውጭ ምንዛሬ ከማዳኑም በላይ የጤና ቱሪዝም መስፋፋት ለሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለሆቴሎችና ለትራንስፖርት ዘርፍ የሚፈጥረው ዕድል ከፍተኛ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ከሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የጤና ቱሪዝም አሁን ከደረሰበት ደረጃ ይበልጥ በማጠናከር የከተማዋን ስማርት ሲቲ የማረጋገጥ ጉዞ እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብሏል። በተጨማሪም የነባር ሆስፒታሎችን ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ዘመናዊ አዳዲስ ሆስፒታሎችን ግንባታ በፍጥነትና በጥራት በማጠናቀቅ የጤና አገልግሎትን በማሳለጥ ረገድ ረጅም እርቀት መጓዝ ተችሏል።

በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ጭምር ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ጋር እኩል ደረጃ ያላቸው ጤና ጣቢያዎች በውስጥ አቅም ከፍተኛ በጀት በመመደብ በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ እና ሙያዊ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች ጭምር እንዲደራጁ ማድረግ ስለመቻሉም ቢሮው ይገልጻል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review