AMN ሚያዝያ 15/2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ጠዋት የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት ከዶክተር ዣን ካሴያ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።
በውይይታችን በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የመከርን ሲሆን፤ በተለይም በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) በመሆን የተሰጠኝን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረናል ሲሉም ገልጸዋል።
የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጤናው ዘርፍ የሚገጥመንን ተለዋዋጭ ተግዳሮቶች ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ዐቅም መጠቀም የጤና ሥርዓታችንን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋት እና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ታረጋግጣለች ሲሉም ገልጸዋል።
ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ (Africa CDC) እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ ነኝ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመልዕክታቸው።