የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ-ብዙ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ከንቲባዋ በምልከታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ከተማዋን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በብዝኀ-ዘርፍ ስትራቴጂ የሚመሩና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።
ልማቱ የቱሪዝም፣ የአካባቢ ጥበቃና የከተማ ግብርናን ያቀናጀ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ በተለይም በወንዝ ዳርቻዎች የለሙ የፍራፍሬ ፓርኮችና የንብ ማነብ ሥራዎች ለምግብ ዋስትናና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም በእንጦጦ ተራራ ሥር የሚገነባውን ስታዲየም ጨምሮ በዚሁ መስመር የሚገኙ 15 የስፖርት ሜዳዎች ለሀገራዊ የእግር ኳስ ዕድገት መሠረት እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት የተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፤ በወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ብቻ ለ56 ሺህ ዜጎችና ለ300 ማኅበራት የሥራ ዕድል መፈጠሩንና ስምንት ወንዞች ባማረ ሁኔታ መልማታቸውን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ አክለውም ወደ ወንዝ ፍሳሽ መልቀቅ ወንጀል መሆኑን አሳስበው፤ ሕዝቡ አካባቢውን ከብክለት በመከላከል የባለቤትነት ስሜት እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና የዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ፣ ከተማዋን የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በበረከት ጌታቸው