አይሾው ስፒድ እስከ ዲዲጂ – የጥቁር አሜሪካውያን የስበት ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ

You are currently viewing አይሾው ስፒድ እስከ ዲዲጂ – የጥቁር አሜሪካውያን የስበት ማዕከል የሆነችው ኢትዮጵያ

ባለፉት አሰርት ዓመታት የምዕራባውያን ትላልቅ ሚዲያዎችና የኃይል መዋቅሮች በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር በማውጣት አፍሪካን የድህነት፣ የረሃብና የትርምስ ማዕከል አድርገው ሲስሏት ቆይተዋል። ይህ ስልታዊ ፕሮፓጋንዳ ዓላማው አፍሪካን ከአሕጉሪቱና በዲያስፖራ ካሉ ቤተሰቦቿ መነጠል፣ በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን በ”እናት አሕጉራቸው” እንደ ባዕድ እንደሚታዩ ማሳመን ነበር።

የሀሰት ግንብ መፍረስ

ሆኖም ግን ይህ ለብዙ ዘመናት የተገነባ የሀሰት ግንብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ባሏቸው ወጣት ዲጂታል ተጽዕኖ ፈጣሪዎች አማካኝነት በ60 ሰከንድ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እየፈረሰ ይገኛል። አሜሪካዊው ዝነኛ ዩቲዩበር እና የቀጥታ ስርጭት (Live Streamer) ባለሙያ አይሾው ስፒድ (IShowSpeed) አፍሪካን መጎብኘቱ ለተለመደው የምዕራባውያን ትረካ “ድንገተኛ” ክስተት ሆኗል። ድንገተኛነቱም ዓለምን በተሳሳተ መንገድ ሲስል የኖረውን የፕሮፓጋንዳ ግድግዳ በማፍረሱ ነው።

ከማስጠንቀቂያ ወደ ጥሪ

ስፒድ እንደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒኣ፥ ማላዊ እና አንጎላ ያሉ ሀገራትን ሲጎበኝ የታየው እውነታ ከሚነገረው ተቃራኒ መሆኑን ነው። በሔደበት ሁሉ ወደር የሌለው ፍቅር፣ ክብርና በረከት አግኝቷል። አንዳንዶች ይህ ፍቅር የታዋቂነቱ ውጤት ነው ቢሉም፣ ስፒድ በአውሮፓ እና በኤዥያ ጉዞዎቹ የዘረኝነት ስድብና የሙዝ ውርወራ ሲገጥመው እንደነበር ይታወቃል።

በአፍሪካ ግን ዝነኛ ብቻ ሳይሆን ተወዳጅ ወንድም መሆን ችሏል። ይህ ጉዞ ትልቅ ተጽዕኖ የፈጠረው ተከታዮቹ አዳዲስ ወጣቶች በመሆናቸው ነው። ስፒድ መልዕክቱን “ተጠንቀቁ” ከሚለው ማስጠንቀቂያ ወደ “ኑና እዩት” የሚል ጥሪ ቀይሮታል።

የራፐር ዲዲጂ (DDG) የኢትዮጵያ ጉዞ ጉጉት

የአይሾው ስፒድ ጉዞ በፈጠረው ታላቅ መነቃቃት ከተሳቡ ዝነኞች መካከል አንዱ አሜሪካዊው ራፐርና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪው ዲዲጂ (DDG) ነው። በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾቹ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ተከታይ ያለው ዳረይል ድዋይኒ ግራንቤሪ (DDG) ኢትዮጵያን የመጎብኘት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው በይፋ አስታውቋል።

ዲዲጂ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ቀድሞም ቢሆን በሀገሪቱ ባሕልና ዕሴት በመማረኩ ሲሆን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ባሕላዊ ውዝዋዜ (እስክስታ) በመሞከር ለተከታዮቹ አጋርቷል፥ የኢትዮጵያን ባሕላዊ ምግብ “እንጀራ በወጥ” በመቅመስ ምን ያህል ጣፋጭና ተወዳጅ መሆኑን መስክሯል።

የማኅበራዊ ሚዲያ መነቃቃትና የቱሪዝም ዕድል

ሆኖም ግን የአይሾው ስፒድን የቀጥታ ስርጭት ከተመለከተ በኋላ ከፍተኛ መነሳሳት ስለተፈጠረበት ዲዲጂ በኤክስ (X) ገጹ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎቱን አጋርቷል። ልጥፉም ከ730 ሺህ በላይ ዕይታን አግኝቷል። በርካታ ተከታዮቹና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ጉዞውን እንደሚደግፉና ምድረ ቀደምት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆንለት እያበረታቱት ይገኛል።

ይህ የዝነኞች ፍላጎት ኢትዮጵያ ለዓለም የምታሳየው ሌላ ገጽታ እንዳላት በተግባር የሚያስመሰክር ሆኗል። አይሾው ስፒድ እና ዲዲጂ እያደረጉ ያሉት ከቪዲዮ መቅረጽ ባለፈ፣ ቀጣዩን ትውልድ ከአፍሪካ ጋር በክብር፣ በፍቅር እና በዕውነተኛ ምስል ማገናኘት ነው። የዲዲጂ ጉዞ ዕውን ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ዕምቅ ሀብት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።

በሚካኤል ህሩይ እና በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review