AMN — ነሀሴ 15/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በመከላከያ እና ደህንነት መስኮች ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለመመስረት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተመራ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎችን ያካተተ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአሜሪካ ከነሐሴ 13 እስከ 14/2018 ዓ.ም ጉብኝት በማድረግ በፔንታጎን ከአቻዎቻቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካ ጦር ሚኒስቴር አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ የጋራ ምክክሮችን አድርገዋል።

የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት የመከላከያ ሚኒስትር ብራያን ጄ. ኤሊስ ጋር በጋራ በተመራ ምክክር የሁለቱን አገራት ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብሮችን ወደ አዲስና የላቀ ምዕራፍ ለማሸጋጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
የሁለቱም አገራት የመከላከያ ተቋማት አመራሮች የተቋማቱን ትብብር ለማስፋት እና ስትራቴጂካዊ ቅንጅትን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ ስትራቴጂካዊ ትብብሩ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅምና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የጋራ መተማመንን በማጠናከር ዘላቂ ትብብር መመስረት እና በአፍሪካ ቀንድ እና በሰፊው ቀጣና ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት እና መረጋጋትን ለማስፈን የጋራ ጥረቶችን ለማሳደግ ዓላማ በሚያደርግ ዋና ዋና ምሰሶዎች የሚመራ ነው።

ሜጀር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ እና ምክትል ረዳት ሚኒስትር ብራያን ጄ. ኤሊስ የተደረሱትን ማዕቀፎች በፍጥነት ወደ ተግባር ለማስገባት እና የሁለትዮሽ የመከላከያ ግንኙነቱን ወደ ተሻለና ወደፊት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ልዑካን ቡድኑ በቆይታው ወቅት ከሌሎች የአሜሪካ መከላከያ ተቋማት አመራሮች ጋር ሰፊ ውይቶችን ከማድረጉ ባሻገር ጉብኝቶችን ማካሄዳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡