AMN ጥር 23 / 2018 ዓ.ም
በ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አርሰናል በኤላንድ ሮድ ሊድስ ዩናይትድን ይገጥማል፡፡ መድፈኞቹ በሊጉ ያላቸው ሰሞነኛ ብቃት ጥሩ አይደለም ፡፡ ከመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ከሊቨርፑል እና ኖቲንግሃም ፎረስት በተመሳሳይ 0ለ0 ሲለያዩ ፣ በማንችስተር ዩናይትድ 3ለ2 መሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
መሪነታቸውን የበለጠ የሚያሰፉበትን እድል አለመጠቀማቸው መጠነኛ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ ሦስት ነጥቡን መውሰድ እንደግዴታ እየተቆጠረ ይገኛል።
በቅርብ ዓመታት ከሊድስ ጋር ያለው የበላይነት ለአርሰናል ትልቅ ተስፋ ይሰጠዋል፡፡ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ያደረጋቸውን ስድስት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎችን በሙሉ አሸንፏል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች 20 ግብ አስቆጥሮ አምስት ግብ ብቻ ተቆጥሮበታል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር በኤምሬትስ ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል 5ለ0 መርታቱ ይታወሳል፡፡
ሊድስ በሜዳው አርሰናልን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈው እኤአ 2000 ላይ ሲሆን በወቅቱ ሃያል የነበረው ሊድስ 1ለ0 አሸንፎ ነበር፡፡
ሊድስ ዩናትድ ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ የሚባል ነው ፤ ከመጨረሻ 10 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ነው የተሸነፈው ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት በሜዳው ኤላንድ ሮድ አርሰናልን ሲያስተናግድም ለተጋጣሚው ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ኒውካስትል ዩናይትድን ምሽት 5 ሰዓት ያስተናግዳል።
ከዋንጫ ፉክክር ርቆ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እየተጋ የሚገኘው ሊቨርፑል ካለፉት አምስት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አንድም ማሸነፍ አልቻለም።
ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ዌስትሃም ዩናይትድን የሚያስተናግድበት የለንደን ደርቢ ጨዋታ ሌላው ተጠባቂ ፍልሚያ ነው።
በሁሉም ውድድር አራት ተከታታይ ድል ያስመዘገበው የሊያም ሮሲኒኦር ቡድን ጥሩ መነቃቃት ላይ ከሚገኘው ዌስትሃም ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል። ጨዋታው ምሽት 2:30 ይጀምራል።
ብራይተን ከ ኤቨርተን ፤ ዎልቭስ ከ ቦርንማውዝ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት የሚጀምሩ ጨዋታዎች ናቸው።
በሸዋንግዛው ግርማ