AMN ጥር 26/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር ተያይዘዉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የቤት ልማት ፖሊሲ በቅርቡ መጽደቁን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በመንግስት፥ በግል፥ በመንግስትና በግል አጋርነት 1.5 ሚሊየን ቤት ለመገንባት ሰፋፊ ስራዎች መጀመራቸዉን ተናግረዋል፡፡

የቤት አልሚዎችና ገዢዎች ከባንኮች ጋር በመዋዋል ቤት የሚያለሙበት የሞርጌጅ የአሠራር ስርዓት ኢትዮጵያ ዉስጥ እስካሁን ድረስ አለመኖሩን በማንሳት ቤት አልሚዎችም ሆኑ ቤት ገዢዎች ሳይጎዱ ከባንኮች ጋር ተዋዉለው ቤት የሚያገኙበትን አሠራር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አሠራሩን በኢትዮጵያ ዉስጥ ለመተግበር የባንክ፥ የመሬት፥ የዲዛይን፥ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ፖሊሲም እየተዘጋጀ ነዉ ብለዋል፡፡
የሞርጌጅ የአሰራር ስርዓትን ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲጠናቀቁ ይፋ እንደሚደረግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ