• 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና አካታች እንዲሆን መንግስት አብክሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል
• በ2018 በጀት ዓመት በስድስት ወራት 9 ነጥብ 3 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡን ገልጸዋል
ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ በለውጥ ሂደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በተለይ በቅርብ ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተሰሩ ስራዎች ከሀገር ባለፈ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸራቸውና ትኩረት ያገኙ ናቸው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን፣ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ የከተሞችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉን፣ አረንጓዴ አሻራን፣ ስንዴና ሌሎች የከተማ ግብርና ምርቶች ምርታማነት ማሳደግን እና ቴክኖሎጂ ልማትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡
ሰላምና ፀጥታ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ህግ ከማስከበር ባሻገር በሀገራዊ የምክክር መድረክ፣ የሽግግር ፍትህና ሌሎች መንገዶችን በመዘርጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ከምክር ቤት አባላትም ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በአንዳንድ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች የታጠቁ ሀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ በምክክሩ ሂደት እንዲሳተፉ ከማድረግ፣ በምክክሩ ሂደት የትግራይ ክልልን ከማሳተፍና የክልሉ አሁናዊ የሰላም ሁኔታ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ ጋር በተያያዘ ስለተሰራው ስራ የሚለው ይገኝበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ በኢትዮጵያ ለሰላም እጦት አንደኛው ምክንያት የሀሳብ ልዩነትን ከንግግር ይልቅ በሀይል የመፍታት ባህል መኖሩ ነው፡፡ የባንዳነት ባህልና የኢትዮጵያን እድገትና ብልፅግና የማይመኙ ጠላቶች የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነትም የሰላም እጦት ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ተመጋጋቢ ሆነው የኢትዮጵያን እድገትና አብሮነት እየተፈታተኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህልውና የሚገዳደርን ጉዳይ ለመመከት በጋራ መቆም የፖለቲካ ስብእናን እንደማያሳጣ የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን “ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች የኢትዮጵያን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የውጭ ሀይሎች በተለያዩ መልኩ እንደሚንቀሳቀሱ የአደባባይ እውነታ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ከሚያቀርበው ክስ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ከተፈጠረ በኋላ እንደገና ወደ ቅራኔ የተገባው የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በር ጥያቄ ከማንሳቱ አስቀድሞ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል የግለሰቦችን ቤት በማፍረስ፣ ወጣቶችን በመረሸን፣ ፋብሪካዎችን ነቅሎ በመውሰድና በማፍረስ ያደረሰው ጥፋት ከኢትዮጵያ ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት የኤርትራ ሰራዊት ወደ መቀሌ በመግባት ተጨማሪ ጥፋት እንዳያደርስ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሰላም እንዲመጣ ያደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም የኤርትራ መንግስት ‘ህወሓት ሳይጠፋ ለምን ስምምነት ተደረሰ’ በሚል ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል፡፡ አሁን ግን በትግራይ ክልል ስንት ጥፋት ካደረሰው ሀይል ጋር አብሮ ለመስራት አንዳንድ የህወሓት ሰዎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ይህም የህዝባቸው በደል የማይሰማቸው የመሆናቸው ማሳያ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ከህወሓት ጋር በነበረው ጦርነት መንግስት በኤርትራ ወታደር ዘረፋ እንዳይፈፀም ጥረት ሲያደርግ፣ ህወሓት ግን አማራ ክልል ሲገባ ፋብሪካዎችንና ትምህርት ቤቶችን አፍርሷል፤ ዘርፏል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግን መቀሌ በነበረበት ወቅት የፈረሰ አንድም ቤት እንዳልነበረ አንስተው በስሜት የሚደረግ የፖለቲካ ስራ ድል የማያመጣና በታሪክ ሳይቀር ተጠያቂ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡
ሌላው አማፂ ቡድን ሸኔ መንግስትን ‘አሀዳዊ’ እያለ ሲከስ ኖሮ ዛሬ ግን ከማያምንበት ሀይል ጋር አብሮ እየሰራ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ይህ ዓይነት አካሄድ አዋጪ አይደለም ብለዋል፡፡
“የእኛ ምርጫ በዘላቂነት ነገን በሚፈውስ ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም ለማሳደግ በኢኮኖሚ እድገትና ተቋም ግንባታ ላይ እየተሰራ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያ አየር ሀይል ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በአየር ላይ መብረር የሚችል አንድ ቢጫ አውሮፕላን ብቻ ነበረው፡፡ ዛሬ ግን የተለያየ ስምና ተግባር ያላቸው ከ100 በላይ አውሮፕላኖች ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ ሀይሎች ታጣቂዎችን በገንዘብ በመደገፍ የሚረዱ ቢሆንም አያሸንፉም፡፡ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ ለሚፈልግ ሀይል በራችን ክፍት ነው፤ ኢትዮጵያን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ መንግስት በይቅርታ ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ፣ አማራና በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እየገቡ ይገኛሉ፡፡
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ መንግስት ምን እየሰራ ይገኛል የሚለው ከምክር ቤት አባላት የቀረበ ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽም፣ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም አካባቢ ሰርተውና ተንቀሳቅሰው የመኖር ህገ መንግስታዊ መብት አላቸው፡፡ በራያ፣ በፀለምት፣ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎችም የተፈናቀሉ ሰዎች ተመልሰው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ እስከአሁን ተፈናቃዮች ያልተመለሱበት የወልቃይት አካባቢ ነው፡፡ ይህም የተፈጠረው ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እንደመያዣ ወይም የራስን ህልውና ማቆያ ያደረገ ፖለቲካ በመኖሩ እንደሆነ አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት፣ ከወልቃይት የተፈናቀሉ ወገኖች በወልቃይት ተመልሶ የመኖር መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን ወልቃይት የ‘ይገባኛል’ ጥያቄ በአማራና በትግራይ ክልሎች ይነሳበታል፡፡ የፌዴራል መንግስት የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲመለሱ፣ የአካባቢው ህዝብ ራሱን እንዲያስተዳድርና ወደየት ክልል መሆን እንዳለበት ራሱ መወሰን እንዳለበት ያምናል፡፡ በህዝበ ውሳኔ በህገ መንግስቱ መሰረት እልባት እንዲሰጠው ነው የሚፈልገው፡፡ በዚህ ረገድ ፓርቲዎች አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት አለባቸው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በፌዴራል መንግስትና ህወሓት መካከል የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ፍቱን መድኃኒት እንደሆነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የፌዴራል መንግስት የገባውን ግዴታ ተወጥቷል፤ በትግራይ በኩል ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ረገድ በከፊል ተከናውኗል፡፡ የትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካው አውድ ውስጥ መድረክ እንጂ ተዋናይ መሆን አልቻለም፡፡ ከመድረክነት ወጥቶ የፖለቲካ ተዋናይ ለመሆን በአዲስ መልኩ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከአጃቢነት በመውጣት መሪ ተዋናይ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
ሀገራዊ ምርጫ
በዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተለያየ መልኩ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል፡፡ ከምክር ቤቱ አባላትም መጪው ሀገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲከናወን መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ ነው የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፤ “ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ አካታች፣ ከባለፈው ምርጫ በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንዲሆን አበክረን እየሰራን ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልሴ በውጤት እንየው ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ባለፈው ምርጫ ሲደረግ ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በአደባባይ መከበራቸውንና ምርጫውንም ለማካሄድ ሰላማዊ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክር
ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ከማድረግ አኳያ ለዘመናት በጦርነት ውስጥ ኖረናል፤ የአሁኑ ትውልድ በውይይት ሀገረ መንግስቱን ማጠናከር ይጠበቅብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ከዚህ አኳያ ሁሉም አካል ለምክክር መዘጋጀት አለበት። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስከአሁን 100 ሺህ ሰዎችን አወያይቷል፡፡ የምክክር አጀንዳ ማሰባሰብና በምክክር ጉባኤ ላይ የሚሳተፉትን የመለየት ስራ ተከናውኗል። በትግራይ ክልልም ከተለያዩ አካላት ጋር ከአስር ጊዜ በላይ ስብሰባዎች ተደርገዋል። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዩን ለይቷል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩን ከማድረግ የሚያስቆም ምንም ነገር የለም፡፡ በምክክሩ ሂደት ያልተሳተፉ አካላትም አሁንም ለመሳተፍ በሩ ክፍት ነው፡፡ የምክክሩ ሂደት በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቀሪ ስራዎች እንዲጠናቀቁ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በሚመለከት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራርያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በማብራሪያቸው፤ ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ባደረገችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷን ገልፀዋል። “ኢትዮጵያ ያሳየችው የኢኮኖሚ እድገት በማንም መመዘኛ ፊት አከራካሪ አይደለም” በማለትም ዕድገቱን ገለልተኛ የሆኑ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ያረጋገጡት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ከያዛቸው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ማረጋጋት፣ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎችን ከግብርና መር ወደ ብዝሃ ዘርፍና ብዝሃ ተዋናይ በማሸጋገር ጥራት ያላው እድገት ማስመዝገብ፣ የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ማቃለል የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሁሉም መመዘኛዎች በኢትዮጵያ አመርቂ የኢኮኖሚ ስኬት መመዝገቡን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ “ብዝሃ ዘርፍ” እና “ብዝሃ ተዋናይ” ነው ሲባል፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት በአንድ የሥራ መስክ ወይም በመንግሥት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን፣ በተለያዩ ዘርፎችና በልዩ ልዩ አካላት ጥረት የሚመራ መሆኑን የሚያመላክት ነው። በዚህ የኢኮኖሚ ሪፎርም አማካኝነት እንደ ሀገር እየተመዘገበ ያለው ውጤት፣ ኢትዮጵያን ነዳጅ ሳይኖራቸው ቀዳሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል አንዷ እንድትሆን እንዳደረጋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አንስተዋል፡፡ ይህንን ለማስረዳት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የዕድገት ትንበያ እና አፈፃፀምን እንዲሁም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት የእድገት አፈጻጸም 9 ነጥብ 3 ከመቶ ሆኖ መመዝገቡን፣ ይህም ከዕቅዱ አንፃር ብልጫ ማሳየቱን በመገምገም ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የ10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንድታስመዘግብ የእቅድ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ይህ ትንበያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትንበያ ጋር ተቀራራቢነት አለው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 999 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መሰብሰብ ተችሏል። ይህም ከዓመቱ እቅድ 78 በመቶ የሚሸፍን ነው። በተለይ በሰብል፣ በሆርቲካልቸር እና በጥጥ ምርት ከእቅድ አንጻር 79 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ይህን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ ከእቅድ በላይ ማሳካት እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
የግብርና ግብዓቶች ተደራሽነት በእጅጉ እያገ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም እንደ ሀገር የነበረው 4 ሺህ 700 የትራክተር ቁጥር ወደ 27 ሺህ 200፣ 338 የነበረው የኮምባይነር ቁጥር ወደ 8 ሺህ 700 እንዲሁም 6 ሺህ የነበረው የመስኖ ውሃ ፓምፕ ወደ 280 ሺህ ማደጉን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ ትልቅ የስኬት ጉዞ ውስጥ ስለመገኘቱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለአብነት ዘመናዊ የመስኖ እርሻ መስፋፋት፣ የግብርና ማሽነሪዎችና ቴክኖሎጂዎች በብዛትና በስፋት መሰራጨታቸው፣ የከተማ ግብርናና መሰል ተግባራት እየተለመዱ መምጣታቸው ለስኬቱ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ይጠቀሳል፡፡ በ2017 በጀት ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት በነበሩ ጥቂት ዓመታት በግብርና ዘርፍ የታዩ አፈፃፀሞች ሀገሪቱን ከስንዴ እርዳታ እና ከግዢ የሚያላቅቅ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የ2017 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ ከፍተኛ ምርት የተመዘገበበት ወቅት እንደነበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ፤ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ከቀደመው 2016 ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ24 ነጥብ 7 ከመቶ ጭማሪ ያሳየ ነበር፡፡
በተለይም የስንዴ ምርት እንደ ሀገር የመጣው እመርታዊ ለውጥ አበረታች ስለመሆኑ፤ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረበት የ47 ሚሊዮን ኩንታል ዓመታዊ ምርት መጠን በ2017 በጀት ዓመት ወደ 280 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉ ምስክር ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ ለስንዴ ግዢ የምታወጣውን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማዳን ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ መላክ እንድትጀምር አስችሏታል። ሩዝም በተመሳሳይ ከፍተኛ የምርት ዕድገት እመርታ እየታየበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የኢንዱስትሪውን ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ አይበልጥም ነበር፤ ይህን አሁን በሶስት ዓመት ብቻ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም 16 በመቶ አድጓል። በንቅናቄው አማካኝነትም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ያወጡ የነበሩ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል። ከኢንዱስትሪ የሚገኘው የወጪ ንግድም የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
ያለፉት ዓመታት ሪፖርቶች እና መረጃዎች፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዕድገት በጥሩ ጎዳና ላይ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ለአብነት የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀምን ብንመለከት ኢንዱስትሪው የ10 ነጥብ 1 ከመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከሌሎች ዘርፎች የበለጠ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለዚህ ስኬት “ኢትዮጵያ ታምርት” የተሰኘው ብሔራዊ ንቅናቄ ትልቅ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ተዘግተው የነበሩ 450 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጋቸው የአንበሳውን ድርሻ እንደተጫወተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመትን አፈጻጸም አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡ በዚሁ ዓመት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ45 በመቶ ወደ 56 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል።ሀገር በቀል የሆነው የኢኮኖሚ ሪፎርም አቅም ከፈጠረላቸው ዘርፎች መካከል ማዕድን ይጠቀሳል፡፡ ይህ ዘርፍ በያዝነው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የ30 በመቶ የገቢ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተለይ የብረት ምርት 36 በመቶ እንዲሁም የሲምንቶ ምርት 28 በመቶ ጨምሯል። ለዚህ ደግሞ የቤት ልማት እየተስፋፋ መምጣቱ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል፡፡
የማዕድን ዘርፉ የሀገርን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ አይተኬ ድርሻውን እንዲወጣ ከለውጡ በኋላ የተሠሩ ሥራዎች ማርሽ ቀያሪነታቸው አይካድም። ለአብነት የወርቅ ኮንትሮባንድን ለመቀነስ የወርቅ ግዢ ዋጋ ላይ የተደረገውን ማስተካከያ ጨምሮ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ ከውጭ ይገባ የነበረውን የከሰል ድንጋይ 100 እጅ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ይጠቀሳሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በተሠራው ሥራ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ይወጣ የነበረውን ወርቅ ከ50 በመቶ በላይ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል፡፡ እንዲሁም የድንጋይ ከሰል ምርትን በሀገር ውስጥ በማምረት ቀደም ሲል ለውጭ ግዢ ይወጣ የነበረውን እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ ማስቀረት ደረጃ ላይ መደረሱ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚሰጡት ሀገራዊና ዓለም አቀፍ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ቀጥለዋል። ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንደጠቆሙት፣ በያዝነው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎችን አጓጉዟል፡፡ ይህ አሃዝ ከለውጡ በፊት በነበሩት ጊዜያት በዓመት ከነበረው አፈፃፀም የበለጠ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በለውጡ ጅማሬ በዓመት የሚያጓጉዘው ደንበኞች ቁጥር ወደ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ነበር።
በተመሳሳይ በኢትዮ ቴሌኮም እየተመዘገበ ያለው ለውጥ አበረታች ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት (የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርት እስከቀረበበት) ጊዜ ድረስ እንደ ሀገር የሞባይል ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥር 97 ሚሊዮን ደርሷል።
ይህ አሃዝ በለውጡ ጅማሬ 37 ሚሊዮን ነበር፡፡ የ5 ጂ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥርም በቅርቡ 30 የሚደርስ ይሆናል። የሞባይል ገንዘብ ተጠቃሚ ዜጎች ቁጥርም 58 ሚሊዮን ደርሷል። ይህም የፖሊሲ ትኩረት ውጤት ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም፤ የወጪ ንግድ አፈፃፀም፣ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ አመርቂ ሥራዎች እንደሀገር እየተከናወኑ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት፤ ከሸቀጦች ወጪ ንግድ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል። ይህም ከእቅዱ አንጻር የ120 በመቶ አፈጻጸም ያሳያል። ከአገልግሎት ወጪ ንግድም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሆም ከሃዋላ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በስድስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብም የተሳካ የማክሮ ኢኮኖሚ ስራ ተከናውኗል። በዘንድሮው ዓመት የዋጋ ንረቱን ወደ አንድ አሃዝ (9 ነጥብ 7 በመቶ) ማውረድ እንደተቻለም ገልጸዋል።
ማህበራዊ ጉዳይ
በትምህርት ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ በመቅረፅና ስርዓተ ትምህርት በማሻሻል፣ የመሰረተ ልማቶችን ደረጃ በማሳደግ፣ ቅድመ መደበኛ ትምህርትን በማስፋፋት ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል። ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በተያያዘ የትምህርት ጥራት ላይ በማተኮር ተሰርቷል። ተማሪዎች በዘመኑ እውቀትና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል። በሰላም አለመኖር ምክንያት ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ተማሪዎችን በተመለከተ ልጆች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክል ታጣቂ መኖር እንደሌለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ሌላው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የጤናው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከሚያስፈልገው መድኃኒት 8 በመቶ የሚሆነው ብቻ በኢትዮጵያ ይመረት ነበር። በአሁኑ ወቅት 42 በመቶ በማድረስ ትልቅ እምርታ ማምጣት ተችሏል፡፡ ከመድኃኒት ስርጭት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ “በቅርብ ጊዜ በተሰራው የስነ-ህዝብ እና ጤና ጥናት መሰረት ከአስር ዓመት በፊት ከመቶ ሺህ ከሚወልዱ እናቶች ከ400 በላይ እናቶች ይሞቱ ነበር፤ አሁን ላይ ወደ 141 ቀንሷል፡፡ እንዲሁ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ከ37 በመቶ ወደ 61 በመቶ ማድረስ ተችሏል” ብለዋል። የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል መንግስት በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ሪፎርም እያካሄደ ይገኛል፡፡ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል የሚሰጡበት የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት እስከአሁን 33 የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጥባቸው ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ 100 ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ በተጨማሪ በአውቶብስ በመንቀሳቀስ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተሮች