AMN ሰኔ 7/2018

የቱለማ ኦሮሞ ገዳ ሥርዓት የ71ኛው ዙር የስልጣን ሽግግር ‘ዳካ ኮራ’ በተባለ ልዩ ስፍራ አካሄዷል።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በሜልባ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ሲመራ የነበረው የቱለማ ገዳ ስልጣኑን ለገዳ ሙደና አስረክቧል።

የሙደና አባ ገዳ የሆኑት አባገዳ ጌቱ ተሊላ ቱፋ: አዲሱ የቱለማ አባገዳ በመሆን አለንጌ ተረክበዋል።
የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ለብዙ ዘመናት የዘለቀና ዓለም ያደነቀው የማይዳሰስ ቅርስ ሲሆን፣ ይህ ሥርዓት የማኅበረሰቡን ባህል፣ እሴትና ሥነ-ምግባር ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሻገር ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል።

የተለያዩ ድርሳናት እንደሚያስረዱት ገዳ፤ ሰላምና እርቅን የሚያሰፍን፣ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክር፣ ማንነትንና ባህልን የሚጠብቅ፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ለትውልድ የሚያስተምር ሥርዓት ነው።

ይህንኑ መሠረት በማድረግ፣ የቱለማ ገዳ ሥርዓት የ71ኛውን ዙር የሥልጣን ሽግግር ከ’ገዳ ሜልባ’ ወደ ‘ገዳ ሙደና’ አስተላልፏል።
በዚህ ሥርዓት ላይ አባገዳ ጌቱ ተሊላ ቱፋ ቦኩ ወይም የሥልጣን ማሳያ የሆነውን በትር እና አለንጋ ተረክበዋል።
በስልጣን ሽግግሩ ባህላዊ ስርዓት ላይ ባህላዊ ግብዣዎች፣ ምርቃት፣ የሕዝባዊ ባህል ዜማዎችና ውዝዋዜዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የኦሮሞ ሕዝብ አዲሱን አባ ገዳ በደስታ ተቀብሎታል።
በወንድማገኝ አሰፋ