AMN- የካቲት 6/2018 ዓ.ም
በዘመናዊው ዓለም የኑሮ ፍጥነት መጨመር እና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር ተያይዞ፣ ምግብን አቀነባብሮ ማሸግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።
ይሁን እንጂ ብዙዎቻችን “የታሸገ ምግብ” ሲባል ከጤና መታወክ ጋር አያይዘን የመስጋት ዝንባሌ ይታይብናል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ምግብ መምህርትና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ዘላለም ደበበ ግን፣ የታሸጉ ምግቦች መጥፎ ስም ሊሰጣቸው እንደማይገባና ይልቁንም የምግብ ብክነትን ለመቀነስና ተደራሽነትን ለመጨመር የጎላ ሚና እንዳላቸው ያስረዳሉ።
ዶክተር ዘላለም እንደገለጹት፣ የታሸጉ ምግቦች ዋና ዓላማ ምግብ ሳይበላሽና ሳይባክን ለረጅም ጊዜ ቆይቶ ለብዙ ሰው መዳረስ እንዲችል ማድረግ ነው።
ለምሳሌ ቲማቲም በቆርቆሮ ባይታሸግ ኖሮ፣ በሚሊየን የሚቆጠር ቶን ቲማቲም ባክኖ ይቀር ነበር” ይላሉ። ስለዚህ ማሸግን በጥሩ መንፈስ ማየትና እንደ አንድ ዘመናዊ የምግብ ዝግጅት ዘዴ መቀበል እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ባለሙያዋ የታሸጉ ምግቦችን በዝግጅት ሂደታቸው ላይ ተመስርተው በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች ያስቀመጧቸው ሲሆን፣ ይህም ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን የጠበቁ፣ ተቀናብረው የሚወጡ እና በከፍተኛ ሂደት የሚያልፉ በሚል ይከፍሏቸዋል፡፡
•ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን የጠበቁ ምግቦች፦ እነዚህ በጣም በትንሹ የተቀነባበሩ ምግቦች ናቸው። ለምሳሌ ፓስቸራይዝድ ተደርጎ በላስቲክ የታሸገ ወተት ባክቴሪያ እንዳይኖረውና ሰውን እንዳያሳምም ተብሎ የሚዘጋጅ እንጂ ወተቱን መጥፎ አያደርገውም። ቲማቲም ታጥቦና ተከታትፎ ቢታሸግም ተፈጥሮአዊ ይዘቱ አይቀየርም።
•ተቀናብረው የሚወጡ፦ እንደ ዘይት ያሉ ምርቶች ከኑግ ወይም ከሱፍ ተቀናብረው ሲወጡ ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን ቢቀይሩም፣ ለብዙሃኑ ተደራሽ እንዲሆኑ ተብለው የተሰሩ መሆናቸውን ያብራራሉ።
እዚህ ላይ ችግሩ ምርቱ ሳይሆን አጠቃቀማችን ነው የሚሉት ባለሙያዋ፣ ሥራን ስለሚያቀልልን ብቻ ያለ መጠን መጠቀም ለጤና ጠንቅ ሊሆን ይችላል በማለት ያስረዳሉ።
•ከፍተኛ ሂደት ያለፉ ምግቦች፦ ትልቁ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እዚህ ደረጃ ላይ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ የድንች ቺፕሶች የሚሰሩት ድንቹ ተፈጭቶ፣ ከብዙ ኬሚካሎች፣ ማቅለሚያዎችና ሰው ሰራሽ ሽታዎች ጋር ተቀላቅሎ ድንች እንዲመስል ተደርጎ ነው።
የታሸጉ ምግቦች ውስጥ የሚጨመሩ እንደ ጨው፣ ስኳር እና ማቆያ ያሉ ንጥረ ነገሮች ያለ ገደብ የምንጠቀማቸው ከሆነ ከፍተኛ የጤና ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል።
ህብረተሰቡ የታሸጉ ምግቦችን ሲገዛ መለያውን (Label) በጥንቃቄ እንዲያነብ ዶክተር ዘላለም ይመክራሉ።

ይህም አንድ ሰው በቀን የሚጠቀመው የስኳር እና የጨው መጠን ይህን ያህል መሆን አለበት ብሎ ከወሰነ፣ በቲማቲም ድልህ ውስጥ ያለውን የጨው መጠን አይቶ ውሳኔውን ለማስተካከል ይረዳዋል ይላሉ።
በተለይ ጨው፣ ስኳር እና ቅባት በብዛት የሚገኙባቸው የታሸጉ ምርቶች ላይ የሚሰፍሩ መረጃዎች ግልጽ መሆን እንዳለባቸውና ተጠቃሚውም ከተፈጥሮ ይዘቱ ምን ያህል እንደራቀ ማስተዋል እንዳለበት ያስረዳሉ። በአጠቃላይ የታሸጉ ምግቦች የሰው ልጅን ድካም የሚቀንሱ እና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ጠቃሚ ግኝቶች ናቸው።
ሆኖም ግን፣ “የታሸገ ሁሉ ምግብ ነው” በሚል እሳቤ እንደ ድንች ቺፕስ ያሉ ከፍተኛ ኬሚካል ያለባቸውን ምርቶች ደጋግሞ በብዛት መጠቀም፣ የተጨመረባቸውን ጨው፣ ስኳር፣ ቅባት እና ኬሚካሎችንም አብረን እንደምንጠቀም አስተውለን አለማዘውተር ይመከራል።
ሚዛናዊ አጠቃቀም፣ የምርቱን ደረጃ ማወቅና በመለያው ላይ ያሉትን መረጃዎች መፈተሽ ለተሻለ ጤና ወሳኝ እንደሆነም ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ቁጥጥር ሕግ ማስፈጸም ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙላቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ማህበረሰቡ የታሸገ ምግብ ሲገዛ ደህንነቱ እና ጥራቱ የተረጋገጠበት የባለስልጣን መሥሪያቤቱ የምዝገባ ቁጥር መኖሩን ማየት እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የታሸጉ ምግቦች ይዘት መግለጫ መረጃዎችን በሚገባ ማንበብ እንደሚያስፈልግ ያነሱ ሲሆን፣ ይህም የአምራቹ ስም፣ የምርት ዘመን እና የሚያበቃበት ጊዜ የመሳሰለውን በደንብ ማጤን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በታምራት ቢሻው