AMN- ሚያዝያ 8/2018 ዓ.ም
የራስ ምታት ህመም ከሌላ የጤና እክል ጋር በተጓዳኝ ወይም ራሱን ችሎ ሊከሰት ይችላል።
ራሱን ችሎ የሚከሰት ራስ ምታት “የመጀመሪያ ደረጃ” ተብሎ የሚመደብ ሲሆን፣ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣው ደግሞ “ሁለተኛ ደረጃ” በመባል ይታወቃል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃው የራስ መርዘን (ማይግሬን) ህመም፣ በመጀመሪያው ደረጃ ውስጥ የሚመደብ የራስ ምታት ዓይነት ነው።
የራስ መርዘን (ማይግሬን) ህመም መንስኤዎችን፣ ምልክቶችንና የሕክምና አማራጮችን በተመለከተ በዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ዮርዳኖስ መንግሥቱ ለኤ ኤም ኤን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የራስ መርዘን (ማይግሬን) ህመም ያለባቸው ሰዎች ዋናው ህመም ከመጀመሩ ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ስሜቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ።
ከእነዚህም መካከል የምግብ ፍላጎት መጨመር (በተለይ ጣፋጭ ምግቦች)፣ በተደጋጋሚ ማዛጋት፣ መነጫነጭ እና መበሳጨት ዋናዎቹ ናቸው።
ህመሙ ሊጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በዓይን ላይ ነጫጭ ነጠብጣቦችና ዝግዛግ ቅርጽ ያላቸው ብርሃናማ ምልክቶች መታየት፣ የሰውነት መደንዘዝ ወይም የመውጋት ስሜት፣ ድምፅን ቶሎ ለመስማት መቸገር እና የንግግር መቆራረጥ ያጋጥማል።
ዋናው ህመም በሚጀምርበት ወቅት ደግሞ ከፍተኛና የመውጋት ስሜት ያለው ህመም የሚኖር ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ጭንቅላትን ለሁለት ከፍሎ በአንድ በኩል ብቻ ያማል።
ከዚህ በተጨማሪም ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ ብርሃንና ድምፅ የመጥላት ወይም የመፍራት ስሜት አብሮ ይከሰታል።
ለራስ መርዘን (ማይግሬን) መነሻ ተብለው ከሚጠቀሱት የሥራ ጫና እና ጭንቀት በተጨማሪ፣ ህመሙን የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች እንደ ግለሰቡ ሊለያዩ ስለሚችል ለይቶ ማወቅን ይጠይቃል።
ከፍተኛ ሙቀት ወይም ቀዝቃዛ አየር፣ አይብ፣ ቸኮሌት፣ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች፣ ሽቶዎች ወይም የኬሚካል ሽታዎች፣ ከልክ በላይ መተኛት ወይም የእንቅልፍ እጥረት ለበሽታው መንስኤ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የራስ መርዘን (ማይግሬን) ህክምና በሁለት የሚከፈል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ህመሙ ሲከሰት ወዲያውኑ ለማስታገስ የሚሰጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ህመሙ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸው ሰዎች የህመሙን ድግግሞሽ ለመቀነስ የሚሰጥ ህክምና ነው።

ሕክምናው በመርፌና በክኒን መልክ የሚሰጥ ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ እስከ ስድስት ወር የሚቆይ የቅድመ-መከላከያ መድኃኒቶችን ሊያካትት ይችላል።
ዶክተር ዮርዳኖስ እንደሚሉት፣ ህመምተኞች የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትዕዛዝ ደጋግመው መውሰድ የለባቸውም ይህ ድርጊት ራሱን የቻለ ሌላ የራስ ምታት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
ራስ ምታቱ ከተለመደው የራስ መርዘን (ማይግሬን) ስሜት ወጣ ያለ፣ ድንገተኛና በጣም ኃይለኛ የሆነ የራስ ምታት፣ ከትኩሳትና ከአንገት መገተር ጋር የመጣ ህመም፣ የእይታ መጋረድ ወይም የሰውነት ክፍል መስነፍ ካጋጠመ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባ ይመከራል።
ቋሚ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል፣ በቂ ውሃ መጠጣት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ህመሙን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ለይቶ ማስታወሻ መያዝ ህመሙን ለመቆጣጠር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ዶክተር ዮርዳኖስ መንግሥቱ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው