ካዎቼ ካውንዳ የቀድሞ የዛምቢያ መሪ ኬነት ካውንዳ ልጅ ናቸው። አባታቸው ኬኔት ካውንዳ የአፍሪካ ህብረት (የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) መስራች አባቶች ከሚባሉት መካከል አንዱ ናቸው። ከአንድ ወር በፊት የዓድዋ ድል መታሰቢያን ሲጎበኙ የአባታቸው ፎቶ ከሚገኝበት የሙዚየሙ ክፍል ሆነው፣ “አባቶቻችን አፍሪካን አንድ የማድረግ ሀሳብ ይዘው በመስራት አሳክተዋል። አሁን ያለነው ልጆቻቸው የእነሱን ህልም ማስቀጠል ካልቻልን፤ አፍሪካን ነፃና አንድ የማድረግ ህልም ከእነሱ ጋር አብሮ ይሞታል፡፡ እነሱ የለኮሱትን ችቦ ይዘን ወደፊት መሄድ አለብን፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የሰው ልጅ በመንፈሱ ጠንካራ ከሆነ የትኛውም ዓይነት ችግር ቢገጥመው ማሸነፍ ይችላል፡፡ ይህ መታሰቢያ የሚያስረዳው ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ጋር ስትዋጋ ሁሉም ፊቱን ቢያዞርባትም መሰናክሎችን ሁሉ በማለፍ ነፃነቷን አስጠብቃ መቀጠል ችላለች፡፡ ይህም አፍሪካውያን ለነፃነት ለሚያደርጉት ትግል መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ አባቶቻችን ቅኝ ግዛትን በማስወገድ ነፃ የሆነ ሀገር አስረክበውናል፡፡ የእነሱ ወራሾች ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል” ሲሉም ካዎቼ ካውንዳ አክለዋል፡፡
ሌላኛው መታሰቢያውን የጎበኙት ማዳራካ ኔሬሬ ይባላሉ፡፡ የታንዛኒያ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ጁሊየስ ኔሬሬ ከአፍሪካ ህብረት (የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) መስራች አባቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ማዳራካ ኔሬሬ ከአንድ ወር በፊት የዓድዋ ድል መታሰቢያን በጎበኙበት ወቅት፣ “መታሰቢያው በጣም ነው የማረከኝ፡፡ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለማስጠበቅ ከኢጣሊያ ጋር ያደረገችውን ጦርነት በተወሰነ ደረጃ አውቀው ነበር፡፡ ከዚህ ጉብኝት በዓድዋ ምን አይነት ዋጋ እንደተከፈለና እንደተሰራ በዝርዝር ተረድቻለሁ፡፡ በእውነት በዚህ የሚታየው ነገር ማንኛውም የአፍሪካ አንድነትን ለሚያቀነቅን (ፓን አፍሪካዊ) ሰው ትልቅ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ነው። የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶችም የአፍሪካውያንን አንድነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን በመታገል ነፃነቷን አስጠብቃ የዘለቀችበት ታሪክ መነሳሻ ሆኗቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
በአፍሪካ የነፃነት ትግልና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) ምስረታ ጉልህ ሚና ከነበራቸው መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የጋና ፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ የልጅ ልጅ ክዋሜ ቶማስ መታሰቢያውን ከጎበኙት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ቶማስ በአስተያየታቸው፣ “ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ወደ አንድነት እንዲመጡ በማድረግ፣ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ እውን እንዲሆን፣ የአፍሪካ ኩራት በመሆን ወሳኝ ሚና ተጫውታለች፡፡ ይህ ጉብኝት ለእኔ ትርጉም ያለውና ታሪካዊ ነው፤ ምክንያቱም አያቴ ኢትዮጵያ በዓድዋ ድል ለአፍሪካ ነፃነትና ከቅኝ አገዛዝ የመላቀቅ ትግል ምልክት መሆኗን ሲናገር የነበረውን ማየት ችያለሁ፡፡ …ለእኔ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ከታሪኬ (ከአያቴ ታሪክ) በመገናኘቴ ክብር ተሰምቶኛል፤ ምክንያቱም እሱ ዘመኑን የቀደመ ሰው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ስመጣ እንደ ጋናዊ ካለኝ የታሪክ ውርሴ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ጋር ያለኝን ትስስር ነው ያየሁት። በመታሰቢያው ውስጥ የአያቴ ፎቶ ተሰቅሎና ታሪኩ ተካትቶ በማየቴ በጣም ክብር ተሰምቶኛል” ሲሉ የፈጠረባቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
ቶማስ እንደገለጹት፣ እነ ክዋሜ ንክሩማህ ካሉ መሪዎች ራሳችንን የቻልን ነፃ ህዝቦች እንዴት መሆን እንዳለብን መንገዱን አሳይተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ አንድነታችንን ማጠናከርና በኢኮኖሚ ረገድ የራሳችንን ሀብት መጠቀም፣ በራሳችን መተዳደር ከቻልን አፍሪካውያን ድምፃችን የሚሰማና ተፅዕኖ መፍጠር የምንችል እንሆናለን፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ ሊወራት የመጣውን የኢጣሊያን ሰራዊት በዓድዋ ያሸነፈችበትና ድል ያደረገችበት ቀን ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ልዩ ቀን ነው። ድሉ የኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ ከማስቻሉ ባሻገር በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የነበሩ አፍሪካውያንና በመላው ዓለም የሚኖረው ጥቁር ህዝብ ለነፃነቱ የሚያደርገው ትግል እንዲጠናከር መነሳሻ ሆኗል፡፡
የዓድዋ ድል የአፍሪካ፣ የመላው ጥቁርና ጭቁን ህዝቦች የተነሳሽነትና ኩራት ማሳያ ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት በሚገባው ልክ ታውቆ እየተዘከረ አልነበረም፡፡ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት ድሉን በሚመጥን ልክ የሚዘከርበት ታላቅ መታሰቢያ በአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ ላይ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። መታሰቢያውን ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያንና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚመጡ ዜጎች እየጎበኙት ይገኛሉ፡፡
ከቀድሞ የላይቤሪያዋ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የቀድሞ የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱክሴስ ማስራ ጀምሮ ለተለያዩ ጉባኤዎች ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች ልጆችና የልጅ ልጆች፣ ወጣቶች፣ በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያንና የካሪቢያን ተወላጆች እንደጎበኙት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቅኝ ሊገዛት በመጣው ኢጣሊያ ላይ በዓድዋ ያስመዘገበችው ድል በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የነበሩ አፍሪካውያን ‘እኛም ማሸነፍ እንችላለን’ የሚል መነሳሳትና ወኔ እንዲሰንቁ አድርጓል፡፡ አፍሪካውያን የነፃነት ታጋዮች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ኢትዮጵያ እንዴት ቅኝ ግዛትን እንዳሸነፈች ተምረዋል፡፡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በስልጠናም ከኢትዮጵያ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ መታሰቢያው ለአፍሪካውያን ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በተለያየ ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች፣ የቀድሞ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሪ የሆኑ ቤተሰቦች ጎብኝተውታል። ‘ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መፈለግ’ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ወደ መሬት ለማውረድ መሰረት የሆነ፣ አይቻልምን በይቻላል የቀየረ፤ የአፍሪካ መልክ በሌላ የታየበት ድል ነው፡፡
አፍሪካውያን፣ የፓን አፍሪካኒስት ልጆችና የልጅ ልጆች ወደ መታሰቢያው በመጡ ጊዜ “እናንተ የዓድዋ አምባሳደሮች ናችሁ” በማለት መታሰቢያውን ሌሎች አፍሪካውያን እንዲጎበኙ እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አሁንም የማስተዋወቁ ስራ በቂ አይደለም፡፡ ‘ታሪክህን ራስህ በትክክል ካልተናገርክ ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ታሪክህን ይነግሩሃል’ እንደሚባለው አሁንም መስራት ይጠበቅብናል፡፡ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም፣ የማህበራዊ ሚዲያ ሰዎችን (ለምሳሌ በቅርቡ ታዋቂው ዩቲዩበር አይሾውስፒድ ዓድዋን ጎብኝቷል) በመጠቀም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ፣ የዓድዋ ድል ለአፍሪካና ጥቁር ህዝቦች ያለውን ፋይዳ ማስተዋወቅ ተችሏል። ወደፊትም ብዙ እንደሚሰራ ዮሴፍ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በመታሰቢያው የሚገኙ አፍሪካን የሚወክሉ አሻራዎች
መታሰቢያው በውስጡ የዓድዋ ድል እንዴት እንደተገኘ፣ የአፍሪካን የትግል፣ ተጋድሎና ነፃነት ታሪክ የሚያሳዩ ወካይ ምልክቶች፣ ቅርሶች፣ የጽሑፍና የተለያዩ መረጃዎችን አካትቶ ይዟል፡፡ ወደ ዋናው የመታሰቢያ ህንፃ ከመግባታችን በፊት በተለምዶ አራዳ ህንፃ እየተባለ ከሚጠራው ቀጥሎ ሰው ሰራሽ ፏፏቴ፣ እንዲሁም የመታሰቢያው አካል የሆነ 20 ሜትር ርዝመት ያለው የዓድዋ ድል ሀውልት ይገኛል፡፡ ይህ ግዙፍ ሐውልት መሀከል ላይ ዙሪያውን በተለያየ ቅርጻ ቅርፅ ጀግኖች በጦር ሜዳ ጋሻና ጦር ታጥቀው ሲዋጉና ሲዋደቁ፣ ከላዩ ላይ የአፍሪካ ካርታ ይታያል፡፡
የመታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ሐውልቱ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን አፍሪካ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ ትናንት ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈሉ፣ አሁን ያለችው አፍሪካ በተለያዩ ፈተናዎችና ጫናዎች አልፋ ነገ የተባበረች፣ የለማችና የበለፀገች እንደምትሆን እንዲሁም የአፍሪካ የትናንት ትግል፣ የዛሬ ጉዞና መጻኢ እድሏን የሚያሳይ ነው፡፡
በዓድዋ ድል መታሰቢያው ከፍተኛ አስጎብኚ ትዕግስት ሀንጋሶ፣ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፀችው፣ በድል ሐውልቱ ላይ ከላይ የሚታየው የፓን አፍሪካኒዝም መለያ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት መስዋዕትነት በመክፈል ለአፍሪካ ብርሃን እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ሐውልቱ ለከተማዋ መለያ የሆነ፣ ነዋሪዎችና እንግዶች ተሰባስበው የሚጎበኙት፣ ለታሪክ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ፎቶ የሚነሱበት ስፍራ ሆኗል፡፡
ወደ ዋናው የመታሰቢያው ህንፃ ሲገባ መሀል ላይ፣ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌው ጦርነት የኢጣሊያን ሰራዊት ለማሸነፍ የዘየዱት የጦርነት ስልት መታሰቢያነት ከተሰራው ሰው ሰራሽ ፏፏቴ (ፋውንቴን) ቀጥሎ ባለው ህንጻ ላይ በአሻራ ምልክት በዓድዋ ሙዚየም የአፍሪካ ካርታ ቅርፅ በትልቁ ይታያል፡፡ ይህም የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የብርሃን ጮራ የፈነጠቀ መሆኑን ለማሳየት የተቀመጠ እንደሆነ ዮሴፍ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
በመታሰቢያው ከፍተኛ አስጎብኚ ትዕግስት ሀንጋሶ እንደገለፀችልን፣ በካርታው ላይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ አፍሪካ የሚፈነጥቅ ብርሃን የሚታይ ሲሆን ይህም የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን፣ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁርና ጭቁን ህዝቦች ብርሃን መሆን እንደቻለ ያሳያል። ከድሉ በኋላ መላው አፍሪካውያን ይቻላል የሚል መንፈስ በመያዝ ከቅኝ ግዛት ራሳቸውን ነፃ አውጥተዋል፡፡
ሌላው በፓን አፍሪካኒዝም ስም የተሰየመ፣ በመታሰቢያው ከሚገኙ አዳራሾች ሁሉ ግዙፍ የሆነ አዳራሽ አለ። 2 ሺህ 214 ገደማ ወንበሮችን የያዘ፣ የተሟላ የድምፅ ስርዓት የተገጠሙለት፣ አቀማመጡም አቃፊ ዓይነት የሆነ፣ በግዝፈቱም አፍሪካ ከዓለም አህጉራት በስፋት ትልቋ መሆኑን፣ የወንበሮቹ ቁጥር መብዛትም ለብዙሃኑ የአህጉሩ ሀገራት መቀመጫ መሆን የሚችል፣ በአንድነት መሰባሰብ የምንችልበት ቦታ አለን የሚል ምልክት ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም ፓን አፍሪካኒዝም ሲባል የተግባባ፣ የተባበረ የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር ጋር አብሮ የሚታይ እንደሆነ ዮሴፍ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር በሙዚየሙ ከዓድዋ እስከ አፍሪካ ህብረት (የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ምስረታ ድረስ ያሉትን ሁነቶች የሚያሳዩ መረጃዎች የሚገኙበት ክፍል ይገኛል፡፡ የፓን አፍሪካ ኮንግረሶች፣ የፓን አፍሪካኒስቶች እንቅስቃሴ፣ በሁለተኛው የኢጣሊያን ወረራ ጥቁሮች ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙበት ሁኔታ፣ የቀድሞ የአፍሪካ እና የዓለም መሪዎች ኢትዮጵያ በዓድዋ ለአፍሪካ ምን ማለት እንደሆነች ግድግዳ ላይ የሰጧቸው አስተያየቶች ከፎቶአቸው ጋር ይታያል፡፡
ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ በመታሰቢያው የአፍሪካ ህብረትን (የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) በመመስረት አስተዋፅኦ የነበራቸው የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች ታሪካቸው የሚዘከርበት ኮሪደር መኖሩ፣ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንን አንድነት፣ እህትማማችነትና ወንድማማችነት የሚያጠናክር ነው፡፡

ለማሳያነትም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የሰላምና የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ የተናገሩት ንግግር ይገኛል። “የ1896ቱ (እ.ኤ.አ) የዓድዋ ድል የአፍሪካን ህዝቦች አይበገሬነት ያሳየ እና በወቅቱም በመላ አህጉሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ጋር ሲዋጉ ለነበሩ ሁሉ አነሳሽ ሆኗል” ሲሉ መናገራቸው ተከትቧል፡፡ መታሰቢያው ካሉት ሰባት በሮች መካከል መዘጋጃ ቤት በሚገኝበት አቅጣጫ ያለው አንደኛው በር ፓን አፍሪካኒዝም በር በሚል የተሰየመ ነው፡፡
ሌላኛው በመታሰቢያው የዓድዋ ጦርነትን የመሩ 12 የጦር መሪዎች ሐውልት ከግድግዳ ላይ ተሰርቶ የሚገኝ ሲሆን ማታ ላይ በእያንዳንዱ የጦር መሪ አናት ላይ የድል ችቦን የሚወክል መብራት ይበራል፡፡ ይህም የእነሱ መስዋዕትነት ለአፍሪካ ብርሃን መሆኑን ያሳያል፡፡ የጦር መሪዎች ሐውልት ካለበት ህንፃ ፊት ለፊትም የአፍሪካ ካርታ ስዕል ይታያል፡፡ ከፍተኛ አስጎብኚዋ ትዕግስት እንደምትናገረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት እንዲይዝና እንዲጠናከር የዓድዋ ድል ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
መታሰቢያው አፍሪካውያን የዓድዋ ድልን ታሪክ እንዲረዱና ከታሪካቸው ጋር እንዲገናኙ ያስችላል፡፡ ከፍተኛ አስጎብኚዋ ትዕግስት እንደምትገልፀው፣ “አፍሪካውያን መታሰቢያውን ሲጎበኙ በጣም ደስተኛ ናቸው፡፡ የአድዋን ድል የኢትዮጵያ ብቻ ድል አድርገው አይመለከቱም፤ ‘የእኛም ድል ነው’ የሚል መንፈስ አይቼባቸዋለሁ፡፡ የመታሰቢያ ሙዚየሙን ውበት፣ የታሪኩን ትልቅነት በማየት በጣም ይደነቃሉ፡፡ ብዙዎቹ ታሪኩን ያውቁታል፤ ወደ ራሳቸው በመውሰድ አድዋ አባቶቻቸው ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ በሚያደርጉት ትግል መነሳሳት እንደፈጠረላቸው፣ ኢትዮጵያ ድንቅ የሆነ ታሪክና ህዝብ ያላት ሀገር እንደሆነች ሁሌ ይነግሩናል፡፡”
በቅርቡም የአፍሪካ ህብረት መስራች አባቶች የሆኑት ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ክዋሜ ንክሩማህ፣ ኬኔት ካውንዳ፣ ሙሀመድ ጋዳፊና ሌሎች ልጆችና የልጅ ልጆች መታሰቢያውን መጎብኘታቸውን የምታስታውሰው ትዕግስት፣ “ቅኝ ግዛት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ስላልተገዛችሁ አታውቁም፤ የእናንተ ታሪክ ከቅኝ ግዛት እንድንላቀቅ መነሻ ሆኖናል፡፡ ወደ ሌላው ዓለም ስንሄድም የዓድዋ ታሪክ የእኛም በመሆኑ እንኮራለን፡፡” ይላሉ፡፡
ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የዓድዋ ድል ለአፍሪካና በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ፣ ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ የፈጠረው ተነሳሽነት በሚፈለገው ደረጃ አልተነገረም ነበር፡፡ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ቢችሉም አሁንም ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ውስጥ ብዙ ፈተናዎች እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡ አፍሪካውያን በአንድነት መቆምና መተባበር ካልቻሉ የትናንቱ ዕጣ ፈንታ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ አፍሪካውያንን የሚያሰባስቡ ኮንፈረንሶች እየተካሄዱበት ነው፡፡ መታሰቢያው ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን እና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ የመስፈንጠሪያ ስፍራ ነው፡፡
በስንታየሁ ምትኩ