AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው አዲስ መመሪያ፣ ከካናዳ እና ከብሪታንያ የሚመጡ መንገደኞች እስከ ታኅሣሥ 31 ቀን 2026 ድረስ ያለ ቪዛ ወደ ሀገሪቱ መግባት እንደሚችሉ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ይህ ውሳኔ የቻይናን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃትና ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ዩ ፒ አይ በዘገባው አስነብቧል፡፡
የካናዳ ዜጎች ቀደም ሲል ይከፍሉት የነበረው 140 ዶላር እና አድካሚ የቪዛ ማመልከቻ ሂደት አሁን ላይ ቀርቷል መቅረቱም ተገልጿል፡፡
ይህ ውሳኔ የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር እና የካናዳው ማርክ ካርኒ ባለፈው ወር ወደ ቤጂንግ ካደረጉት የጉብኝት እና የንግድ ውይይት በኋላ የመጣ ነው።
ስምምነቱ ካናዳ የቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንድትፈቅድ፣ ቻይና ደግሞ ከካናዳ የሚገቡ ምርቶች ላይ የጣለችውን የታሪፍ ዋጋ እንድትቀንስ መንገድ ከፍቷል ተብሏል።
ቻይና ከኮቪድ-19 ማዕቀብ በኋላ የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የጉዞ ማዕቀቦችን እያላላች መቆየቷ ይታወሳል።
በአስማረ መኮንን