ውጊያን የሚያስቀር ከተከሰተም በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ‘ኤሊት ፎርስ’ እየገነባን ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ውጊያን የሚያስቀር ከተከሰተም በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ‘ኤሊት ፎርስ’ እየገነባን ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- የካቲት 15/2018 ዓ.ም

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በሐዋሳ ከተማ በተከበረው የልዩ ዘመቻዎች እዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ የምትገነባው የልዩ ኃይል ዋነኛ ዓላማ ሽብርና ጦርነት እንዳይከሰት መከላከል፣ ቢከሰትም በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል መደምደም መሆኑን አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ”ቀይ ቦኔት” ለባሾቹ ዕውቅና በሰጡትበት ወቅትም፣ ጥቃት ከመሰንዘሩ በፊት ዝግጁነትን በማሳየት ውጊያ እንዳይጀመር ማድረግ፣ ውጊያ ከተጀመረ ደግሞ በላቀ ብቃትና ፍጥነት ማጠናቀቅ እና ኢትዮጵያን መገንባት፣ መጠበቅ፣ ማጽናት እና ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገር የልዩ ዘመቻዎች እዝ ቁልፍ ተልዕኮዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የወታደራዊ ዝግጁነቷን እያዘመነች መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ በስልጠናው ረገድ የታየውን ለውጥ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከዚህ ቀደም በምድር፣ በተራራና በጅረት ላይ ብቻ ያተኮረ የነበረው ወታደራዊ ስልጠና፤ አሁን ላይ ወደ ባህር ተሸጋግሯል ብለዋል።

ከውሃ የመሸሽ እና እንደ ባዕድ የማየት ልማድ በታላቁ የሕዳሴ ግድብና በወንዝ ዳርቻ ልማቶች መቀየሩንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ አቅም መጎልበት ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም ዋስትና መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review