AMN የካቲት 17/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ለረጅም አመታት መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄ ሆነዉ ከቆዩ የመልካም አስተዳድር ችግሮች አንዱ የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፤ ግልጽ እና ከብልሹ አሰራሮች የጸዳ አለመሆኑ ነዉ፡፡
አገልግሎት ለመስጠት ጉቦ መጠየቅ፣ የቅንነት መጓደል፤ ተገልጋዮችን ማንገላታት እና መሰል የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ህብረተሰቡ ከመንግስት ተቋማት የሚፈልገዉ አገልግሎት እንዳያገኝ ትልቅ ማነቆ ሆነዉ ቆይተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል እና የተቋም ግንባታን በማጠናከር በዘርፉ የሚታየዉን ዉስንነት ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት መስጠት፤ የሰው ኃይል ማብቃት፤ ስነ-ምግባርን ማሻሻል፤ ግልፅ እና ቀልጣፋ አሰራርን መተግበር የከተማ አስተዳደሩ ዋንኛ የትኩረት ማዕከሎች ናቸዉ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሰራው ጠንካራ እና ተከታታይ ስራ እስካሁን 370 አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሰጡ ማድረግ ችሏል።
ሁለት አዳዲስ “መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት መስጫዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲለሙ በማድረግ ወደ አገልግሎት የገቡ ሲሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ መስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

በተሰራዉ ስራም የነዋሪዎችን ቅሬታ፣ የተገልጋዩን እንግልት፣ ጊዜንና ወጪን በመቀነስ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይን እርካታ በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ተችሏል፡፡
ያልተቀረፉ የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን ለመቅረፍም ተጨማሪ ተቋማትንና አገልግሎቶችን ወደ ማዕከላቱ የማስገባት ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግም በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች ደረጃቸውን የጠበቁ የመሶብ ማእከላት በመገንባት ላይ ያሉ ሲሆን በቅርቡ ወደ አገልግሎት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ከሚያደርገዉ ጥረት በተጨማሪ ተገልጋዮችን በማንገላታትና፣ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ በመጠየቅ የተለያዩ ጥፋቶችን የፈፀሙ አካላትንም ተጠያቂ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ተጠያቂነት ከማስፈን አንፃር በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ብቻ 61 አመራሮች፣ 126 ዳይሬክተር እና ቡድን መሪዎች እንዲሁም 3 ሺህ 542 ሰራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በፈፀሙት ጥፋት ተጠያቂ መደረጋቸዉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤት አባላት ባቀረቡት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ማንሳታቸዉ ይታወሳል፡፡
ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የድርሻቸውን ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉም እየተሰራ ይገኛል፡፡
የመማክርት ጉባኤዎች በየደረጃዉ ተቋቁመዉ ወደ ተግባር የገቡ ሲሆን የመዲናዋ ነዋሪዎች በእንጠያየቅ መድረኮች ጥያቄያቸውን አንስተው በአመራሩ ምላሽ እንዲሰጣቸው በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
የትዉልድ ድምጽ የሆነዉ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአገልጋዩ፣ በዋርካ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ እና በሌሎች ፕሮግራሞቹ ህዝቡ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሃሳብ እንዲያነሳና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ የተቋማት ሥራ ሃላፊዎች ተገቢዉን ምለሽ እንዲሰጡ በማድረግ የህዝብ ቅሬታዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ