እየጎለበተ የመጣው ወዳጅነት

You are currently viewing እየጎለበተ የመጣው ወዳጅነት

“በሁለቱ ሀገራት የወል ፍላጎት ላይ ተመስርተን ትብብራችንን የምናሳድግባቸውን መንገዶች ተመልክተናል

                                                      ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

“ትብብራችን በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል

                                                      የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ

ኢትዮጵያንና እስራኤልን በታሪክ፣ በእምነትና ባህል ያቆራኘችው ንግስት ሳባ እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ንግስት ሳባ ወደ እስራኤል አቅንታ ከጠቢቡ ሰለሞን ቀዳማዊ ምኒልክን መውለዷን ከዚያም ታቦተ ፅዮን ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል ያለው የባህላዊ፣ ኃይማኖታዊና መሰል  ግንኙነቶች ከፍ ማለታቸውም እንዲሁ፡፡

በሌላ በኩልም መፅሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳን) ከዓለም ቋንቋዎች ሁሉ ቀድሞ ከእብራይስጥ ቋንቋ የተተረጎመው ወደ ግዕዝ ነው፡፡ ይህንንም እውነት የዐባይን መነሻ ለማየት በአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ፣ “በግዕዝ እና በእብራይስጥ መካከል ያለው መመሳሰል የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ለማለት ይከብዳል” ሲል በማስታወሻው አስፍሯል፡፡

ይሁን እንጂ የሀገራቱ ግንኙነት በዘመናዊ መልኩ የጀመረው እ.ኤ.አ 1956 በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት እንደሆነ ድርሳናት ዋቢ ይሆናሉ፤ ሀገራቱ በልዩ ልዩ ልማቶች እና የወቅቱን ቀጣናዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ትስስርም በየዘመናቱ እያደረጉ መቀጠላቸውን የታሪክና ስነ ልቦና ባለሙያው አቶ ማህደር ሳልህ ይናገራሉ፡፡

የሁለቱ ሀገራት ዘመናትን የተሻገረው ግንኙነት አሁን ላይ በተለያዩ መስኮች የተጠናከረ ሆኖ ይገኛል። የሀገራቱ ግንኙነት ግን በየዘመኑ በነበሩ መንግስታት ፖለቲካ ርዕዮት ምክንያት ከፍም ዝቅም እያለ ጥንካሬውን አስጠብቆ የቀጠለ መሆኑንም የታሪክ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

በተለይም ዴር ሱልጣንን ጨምሮ በኢየሩሳሌም የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት የሁለቱን ሀገራት ባህላዊ ትስስር በፅኑ መሰረት ላይ ገንብተዋል፡፡ ይህ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ከእስራኤል ሀገረ መንግስት ዳግም መመስረትን ተከትሎም እየጎመራ ስለምመጣቱም የታሪክ ባለሙያው  አብራርተዋል፡፡

ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አማረ ከበደ እንደሚሉት ደግሞ የዘመናዊ የኢትዮ-እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የተወጠነው በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር በ1956 ነው፡፡ ይህ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግስት የተጀመረው የሀገራቱ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂካዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እና የወቅቱን የቀጣናውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ በዚሁ ዘመን የነበረው የሀገራቱ ወዳጅነትና ትብብር በተለይ በወታደራዊ እና በልዩ ልዩ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግን  የኢትዮጵና የእስራኤል ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴካዊ አጋርነት እያደገ እንደመጣም ተናግረዋል።

ለአብነትም በ2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በእስራኤል ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት በተምሳሌትነት ያወሱት የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ወሳኝና ታሪካዊ ምክክር አድረገዋልም ብለዋል።

በወቅቱም ሁለቱ ሀገራት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያም የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጎልበት የሚያስችሉ ስምምነቶችን በኢኮኖሚ፣ በግብርና፣ በውሃ፣ በመስኖ፣ በጤና እና በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጸጥታ ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳዬ እንደሚሉት ደግሞ የሀገራቱ ግንገኙነት በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡ ለአብነትም የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በዘመናዊ ግብርና እና በሌሎች ዘርፎች ተሰማርተዋል። በማምረቻ ዘርፍ በተለይም በጨርቃጨርቅ እና በኬሚካል ኢንዱስትሪዎች፣ በጤናና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ በተለይም በፖታሽ በተለይም በግሪን ሃውስ፣ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ እና መሰል ኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ ከፍ ያለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በንግድ ልውውጥ ረገድ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባትና የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ እስራኤል በስፋት ትልካለች። በአንጻሩ እስራኤል የላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ የግብርና ግብዓቶችን (ማዳበሪያና ኬሚካሎች)፣ የሕክምና መሣሪያዎችን እና የደህንነት ቁሳቁሶችን ለኢትዮጵያ እያቀረበች ስለመሆኑም ምጣኔ ሀብት ባለሙያው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩልም በዓለም አቀፍ ደረጃ በደረቃማ እና በረሃማ አካባቢ ግብርና ስመጥር የሆነችው እስራኤል በዘርፉ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የልማት አጋር ናት። በዘመናዊ መስኖ፣ በፍራፍሬ ልማትን መሰረት ያደረጉ በተለይም በእንስሳት እርባታ እና የወተት ምርታማነት አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያሳደገች ስለመምጣቷም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡

ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አማረ ከበደ ከሰሞኑም የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን ሀገራት ለዘመናት የጸና ወዳጅነት ከፍ የሚያደርግና የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ የሚያጎለብት ነውም ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ባሳለፍነው ረቡዕ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉትን  የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግን በመቀበል በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በውይይቱ ወቅት በተለይም የእስራኤል ተወላጅ የሆኑ የቤተ-እስራኤል ማኅበረሰብ አባላት በሁለቱ ሀገራት መካከል እንደ አንድ ሕያው ድልድይ በመሆን ያላቸውን ሚና ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በበኩላቸው “ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ ለይፋዊ ጉብኝት የመጡትን የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግን ተቀብዬ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል” ያሉ ሲሆን፣ “የኢትዮጵያ እና እስራኤልን ግንኙነት በማጤን በወል ፍላጎታችን ላይ ተመስርተን ትብብራችንን የምናሳድግባቸውን መንገዶች ተመልክተናልም” ሲሉ አክለዋል፡፡

የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በበኩላቸው፣ “በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር እጅግ ድንቅ የሆነ ቆይታ አድርጌለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለው፣ በእስራኤል እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ለማጠናከር በኢኖቬሽን፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በውሃና ኢነርጂ ዘርፎች እንዲሁም ቀጠናዊ ትብብርን ማሳደግን አስመልክቶ ሁለቱን ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡

አክለውም፣ “እስራኤል በመላው አፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት ገለጻ አድርጌለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ ሀገሮች ወሳኝና የእስራኤል ቁልፍ አጋር ሆና ለአስርት ዓመታት የቆየች ሀገር ናት፡፡ ትብብራችን በቀጣናው ዙሪያ ሰላምን፣ አንድነትን እና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል፡፡

የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጉብኝተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት “ዛሬ ማለዳ ለእስራኤል ፕሬዝዳንት ክቡር አይዛክ ሄርዞግ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን እና ለሀገር ሉአላዊነት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች ታሪክን አስጎብኝተናቸዋል” ብለዋል።

አክለውም፣ “ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ለነበራቸው ጊዜ እያመሰገንን፤ በምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ እንዲሁም በውቧ መዲናችን አዲስ አበባ የሚኖራቸው ቆይታ ፍሬያማ እንዲሆን በራሴ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ እመኛለሁ” ማለታቸውም ይታወሳል። የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጨማሪ የሳይንስ ሙዚየምን እና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ጉብኝተዋል፡፡ 

የኢትዮ እስራኤል ጉዳይ ዋነኛው የዚህ ፅሑፍ ማጠንጠኛ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላት የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ መጥቷል። ለአብነትም ከጥቂት ሳምንታት በፊት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የሌሎች ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ማሳያ ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተለያዩ ሀገራት የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ። ለአብነትም ባሳለፍነው ሐሙስ በአዘርባጃን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ያደረጉትን የስራ ጉብኝት አስመልክቶ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ “በአዘርባጃን ባደረግኩት የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ላደረጉልኝ ሞቅ ያለ እና የተከበረ አቀባበል ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

አክለውም፣ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፍ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በነፃ የንግድ ቀጣናዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በአዘርባጃን አቻቸው መካከል በተደረጉ የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ በመመስረት አጋርነታችን በየጊዜው እያደገ መጥቷል። እነዚህ የትብብር ዘርፎች ለሁለትዮሽ ግንኙነታችን መጠናከር መሠረት የጣሉ ሲሆን፣ ዛሬ ባደረግነው ጥልቅ ውይይትም ግንኙነታችንን እና ትብብራችንን ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተስማምተናል” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review