ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች

You are currently viewing ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል፣ የመጽሐፍት እና ሃሳብ ውይይት፣ የሥነ-ጥበብ አውደ ርዕይ፣ የሙዚቃ አልበም ምርቃት፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጽሐፍት

“ምስጉን ሰው”መጽሐፍ  በነገው ዕለት ተመርቆ ለንባብ ይበቃል፡፡ የህይወት ታሪክ ዘውግ የሆነው ይህ መጽሐፍ  ነገ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ባምቢስ ሱፐር ማርኬት አጠገብ በሚገኘው ዲ ሊዮፖል ሆቴል ይመረቃል፡፡

በሌላ መረጃ “ዝሃ” መጽሐፍ በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ልዑል ራስ መኮንን አዳራሽ  ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ አንጋፋው ጸሐፊ ተውኔትና አዘጋጅ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ   ነው፡፡

እንዲሁም በዛሬው ዕለት የመጽሐፍ ፊርማ ሥነ ስርዓት እና ውይይት ይካሄዳል፡፡ ውይይቱ የሚደረገው ከወጣቱ ደራሲ አህመድ ሁስ ጋር ሲሆን የቫዮሊን መርሃ ግብርም መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው ለገሃር ተወልደ ሕንጻ ስር በሚገኘው ጃዕፈር መጻሕፍት መደብር ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ደራሲ አህመድ ሁስ “ጥሪ ወደ ሞት” እና “የሎሚ ጭማቂ ትዝታ” በተሰኙት ስራዎቹ ይታወቃል፡፡

የስዕል ዐውደ ርዕይ

“የዝምታ ወጎች” የስዕል አውደ ርዕይ በመጪው ረቡዕ ለእይታ ሊበቃ ነው። ሰዓሊው ታሪኩ አስራት ሲሆን አውደ ርዕይው የሚከፈተው ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኘው በፈንድቃ የባህል ማዕከል ነው፡፡

በተጨማሪም “ውብ አዲስ”  የተሰኘው የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል። የሰዓሊ ሀሮን ሱሌይማን  ስራ የሆነው “ውብ አዲስ” የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ እየታየ የሚገኘው በጣይቱ የባሕልና ትምህርት ነው፡፡ ዐውደ ርዕይው  የሚጠናቀቀው ግንቦት 23 ቀን  2018 ዓ.ም ነው።

በሌላ መረጃ “ትስስር” የተሰኘው የስዕል ዐውደ ርዕይው በመጪው ማክሰኞ ይጠናቀቃል፡፡ የአብዱልቃድር መሐመድ፣ ኢሳ ታደለ እና ምስለኬ እሸቱ ስራዎች የቀረቡበት ይህ የቡድን የግራፊክስ የስዕል አውደ ርዕይ  እየታየ የሚገኘው በፈንድቃ የባህል ማዕከል ነው፡፡

ሙዚቃ

“ጎምጃ” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበም በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአድማጭ ተመልካች ይደርሳል፡፡ የድምፃዊ ግርማይ በላይ (ግርማይ ራያ)  ስራ የሆነው ይህ አልበም  ዛሬ  ከቀኑ 8:00 ሰዓት መገናኛ አካባቢ 24  በሚገኘው ኮከብ ህንፃ ይመረቃል፡፡ ከምርቃቱ በኋላ የሙዚቃ ስራው በድምጻዊው የዩቱብ ገጽ  ለአድማጭ ተመልካች እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡

የቴአትር መርሃ-ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። ቅዳሜ 7፡30 ሲሆን “12ቱ እንግዶች” ቴአትር እንዲሁም 11፡30 ደግሞ “ሸምጋይ” ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ7፡30 “ንጉሥ አርማህ” ቴአትር፣ እንዲሁም  “እምዬ ብረቷ” የተሰኘው ቴአትር በ11፡30 ላይ ይታያሉ፡፡ በብሔራዊ ቴአትር ለሚታዩ ቴአትሮች ተመልካቾች ጊዜያቸውን ለመቆጠብ በ“ሁሉ በጄ” መተግበሪያ በመጠቀም ትኬቶችን አስቀድመው መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል። በተጨማሪም “ባልቻ አባነፍሶ” ቴአትር እሁድ በ8:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ የሚታይ ሲሆን ትኬት በኦን ላይን የክፍያ ስርዓት መቁረጥ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትር ደግሞ ነገሩ አይቆምም ሐሙስ 11፡30 ሳደታ (በአፋን ኦሮሞ ) እሑድ 8፡00 ሰዓት እንዲሁም የመጨረሻው ፍርድ እሑድ 12፡00 ሰዓት ለቴያትር አፍቃሪያን ይታያል፡፡

በተጨማሪም “አዮ ቦራ” የተሰኘው የአፋን ኦሮሞ የህፃናት ቴአትር ቅዳሜ ጠዋት 4፡00 ሰዓት በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ለእይታ ይቀርባል፡፡ በተመሳሳይ “የሰማይ ልጆች” የተሰኘው ቴአትር እሁድ ጠዋት 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ፍላሚንጎ በሚገኘው በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ይታያል፡፡

በጊዜው አማረ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review